ፕሬዚዳንት ትራምፕ ስለ ግድቡ ያስተላለፉት ያልተገባ መልዕክት ኢትዮጵያውያንን በቁጭት የሚያነሳሳ ነው ... ነዋሪዎች - ኢዜአ አማርኛ
ፕሬዚዳንት ትራምፕ ስለ ግድቡ ያስተላለፉት ያልተገባ መልዕክት ኢትዮጵያውያንን በቁጭት የሚያነሳሳ ነው ... ነዋሪዎች
አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 21/2013 (ኢዜአ) የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን በተመለከተ ያስተላለፉት ያልተገባ መልዕክት ኢትዮጵያውያንን በቁጭት የሚያነሳሳ መሆኑን የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች ገለጹ።
ሕዝቡ ለግድቡ ግንባታ የሚያደርገውን ተሳትፎ በእልህና በቁጭት ተነሳስቶ እንዲጨምር ያደርጋልም ነው ያሉት።
ፕሬዘዳንቱ ባለፈው ሳምንት ታላቁ የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብን በተመለከተያንፀባረቁት አድሏዊ አቋም ኢትዮጵያውያንን አስቆጥቷል።
የፕሬዘዳንቱ አስተያየት ኢትዮጵያውያንን በቁጭት አነሳስቶ በራሳቸው ተሳትፎ እየተገነባ ላለው ግድብ እየተደረገ ያለውን አስተዋጽኦ እንደሚያጠናክር አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ ነዋሪዎች ገልጸዋል።
የፕሬዚዳንት ትራምፕ አስተያየት ከአንድ ትልቅ አገር መሪ የማይጠበቅና አስነዋሪ ድርጊት መሆኑን ነዋሪዎቹ ጠቅሰው፤ ግንባታው በመንግሥትና በሕዝብ አጋርነት የሚካሄድ በመሆኑ በማስፈራራትና በጫና እንደማይቆም ገልጸዋል።
ድጋፋቸውን በማጠናከር ግንባታውን ከዳር ለማድረስ ቁርጠኛ መሆናቸውንም በመጥቀስ፤ ኢትዮጵያውያን ማስፈራሪያና ዛቻ የማይቀበሉና በአገርና በወገን ጥቅም ላይ የማይደራደሩ መሆኑንም ነው ነዋሪዎቹ የተናገሩት።፡፡
አስተያየታቸውን ከሰጡት መካከል አቶ ዓለማየሁ አሰፋ ምንም ነገር ቢመጣ ግድቡን ከመስራት የሚያግድ ነገር አለመኖሩንና ይልቁንም እልህ ውስጥ በመክተት ለመስራት ያለውን ፊላጎት በመጨመር የግድቡን ግንባታ ቶሎ ለማጠናቀቅ የሚያነሳሳ እንደሆነ ገልጸዋል።
የግድቡን ግንባታ ለመደገፍ አስፈላጊውን ሁሉ በማድረግ ለአገራቸው መስዋዕትነት ለመክፈል ዝግጁ መሆናቸውን የተናገሩት ደግሞ ሐጂ ሰይድ አህመድ ናቸው።
የፕሬዝዳንት ትራምፕ ያልተገባ ንግግር የህዳሴ ግድብን እንድንገነባ ሃይል ይሆነናል ያሉት ሌላው አስተያየት ሰጪ አቶ በረከት ፍሰሃ፤ ፕሬዚዳንቱ እንደ አገር መሪ ሊናገሩት የማይገባውን መናገራቸው ትክክል እንዳልሆነ ገልጸዋል።
የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ባለፈው ክረምት 4ነጥብ 9 ቢሊዮን ሜትሪክ ኪዩብ ውሃ በመያዝ የመጀመሪያ ዙር የውሃ ሙሌት ስራ መጠናቀቁ የሚታወስ ነው።