ቀጥታ፡

በአዲስ አበባ ለህዳሴ ግድብ ግንባታ በሩብ አመቱ ብቻ ከ700 ሚሊዮን ብር በላይ ተሰበሰበ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 21/2013 ( ኢዜአ) በ2013 ዓ.ም በአዲስ አበባ ለህዳሴው ግድብ ግንባታ 789 ሚሊዮን ብር ለመሰብሰብ ታቅዶ በሩብ አመቱ ብቻ ከ700 ሚሊዮን ብር በላይ መሰብሰቡ ተገለጸ። 

የአዲስ አበባ የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ህዝባዊ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ምስክር ነጋሽ ለኢዜአ እንደገለጹት ለግድቡ ግንባታ የህዝቡ ድጋፍና እገዛ ተጠናክሮ ቀጥሏል።

በ2013 ዓ.ም በአዲስ አበባ 789 ሚሊዮን ብር ለመሰብሰብ ታስቦ ባለፉት ሶስት ወራት ብቻ ከ700 ሚሊዮን ብር በላይ መሰብሰቡን ገልጸዋል።

ከግንቦት 2012 ዓ.ም ጀምሮ የህዳሴ ግድቡ የገቢ ማሰባሰቢያ ዋንጫ በተለያዩ ክፍለ ከተሞች ሲዘዋወር ቆይቷል።

በዚህም የከተማው ነዋሪዎችና የመንግስት ተቋማት ባደረጉት ተሳትፎ እስካሁን ከተገመተው ገቢ በላይ መሰብሰቡን ተናግረዋል።

ለዚህም ህዝቡ ላደረገው የላቀ አስተዋፆ ምስጋናቸውን ያቀረቡት አቶ ምስክር ይሄው ድጋፍና ተነሳሽነት ተጠናክሮ እንዲቀጥልም ጠይቀዋል።

በገቢ ማሰባሰቢያው በኮልፌ ቀራንዮ ክፍለ ከተማ ብቻ ከ100 ሚሊዮን ብር በላይ የተሰበሰበ ሲሆን 23 ሚሊዮን ብር ደግሞ ቃል መገባቱን  የከፍለ ከተማው የህብረተሰብ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት ሃላፊ ወይዘሮ ማህደር ሃብቱ ገልጸዋል።

ክፍለ ከተማው ዋንጫውን ለአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ማስረከቡንም ገልጸዋል።

የህዳሴ ግድብ ግንባታ የመሰረት ድንጋይ ተቀምጦ ገቢ ማሰባሰብ ከተጀመረ አንስቶ እስካሁን በአዲስ አበባ ብቻ ከ1 ነጥብ 1 ቢሊዮን ብር በላይ መሰብሰቡን መረጃዎች ይጠቁማሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም