ቀጥታ፡

ቃሊቲ ማረሚያ ቤትን የጎበኙት የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽነር በእስር ቤቱ ሁኔታ ላይ ቅሬታ አለመቅረቡን ገለጹ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 21/2013 ( ኢዜአ) በቃሊቲ ማረሚያ ቤት ጉብኝት ያደረጉት የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽነር ዳንኤል በቀለ በእስር ቤቱ ሁኔታ ላይ ቅሬታ አለመቅረቡን ገለጹ። 

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽነር ዶክተር ዳንኤል በቀለ እና የኮሚሽኑ ባለሙያዎች በቃሊቲ ማረሚያ ቤት ያለውን የታሳሪዎች አያያዝ ሁኔታ ጎብኝተዋል፡፡

ኃላፊዎቹ አቶ ጃዋር መሐመድና አቶ በቀለ ገርባን ጨምሮ ከእነርሱ ጋር ከተከሰሱት ውስጥ አቶ ሀምዛ ቦረና፣ አቶ ደጀኔ ጣፋ፣ አቶ ሸምሰዲን ጣሃ እና ጋዜጠኛ መለስ ድሪብሳን፤ እንዲሁም አቶ እስክንድር ነጋ እና አቶ ስንታየሁ ቸኮልንና ከእነርሱ ጋር የተከሰሱትን ወይዘሮ ቀለብ ስዩም እና ወይዘሪት አስካለ ደምሌን፣ በተጨማሪም እነ ጄነራል ክንፈ ዳኘው እና ሌሎችም ታሳሪዎች የሚገኙበትን ሁኔታ ተመልክተዋል፡፡

ታሳሪዎችንና የማረሚያ ቤት ኃላፊዎችንም ለየብቻ አነጋግረዋል፡፡

በጉብኝቱም ታሳሪዎቹ በአካላዊ ደህንነት ላይ እንደሚገኙ፣ አጠቃላይ የእስር ቤቱ ሁኔታና የእስር አያያዝም ተቀባይነት ባለው ደረጃ ላይ እንደሚገኝ መመልከታቸውን ኮሚሽኑ ጉብኝቱን አስመልክቶ ለኢዜአ በላከው መግለጫ አሳውቋል፡፡

የተወሰኑ እስረኞች አስተዳደራዊ እልባት የሚሹ ጉዳዮች ከማንሳታቸው በስተቀር በእስር ቤቱ ሁኔታ ላይ ቅሬታ አለማቅረባቸውን በመግለጫው ተገልጿል፡፡

አስተዳደራዊ እልባት ከሚሹ ቅሬታዎች ውስጥ የሕክምና አገልግሎትና የመድኃኒት አቅርቦት በሚፈለገው ፍጥነት አለመገኘቱ፣ ታሳሪዎች ለፍርድ ቤት ለመላክ የሚፈልጉት አቤቱታ በአፋጣኝ አለመላኩ፣ ለቤተሰብ ጉብኝት በቂ ጊዜ አለማግኘትና የስልክ አገልግሎት በተሟላ ሁኔታ አለመዳረስ ይገኝበታል፡፡

የማረሚያ ቤቱ ኃላፊዎች ለታሳሪዎች የሚያስፈልገውን አገልግሎት በተሟላ መንገድ ለማቅረብ ጥረት እንደሚደረግ፣ የቤተሰብ ጉብኝት ሰዓት በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት የጊዜ ገደብ ቢኖረውም እንደ የሁኔታው እየተሻሻለ መምጣቱን ገልጸዋል፡፡

ኮሚሽኑ ታሳሪዎቹ ያቀረቡትን አጠቃላይ አስተዳደር ነክ ቅሬታዎችና እንዲሁም የተወሰኑ ታሳሪዎችን የሚመለከቱ አስተዳደራዊ ጉዳዮች ላይ ከማረሚያ ቤቱ ኃላፊዎች ጋር በመወያየት የማስተካከያ ምክረ ሀሳቦችን ማቅረቡንና በመፍትሄ ሃሳቦቹም መግባባት ላይ መደረሱን በመግለጫው አስታውቋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም