ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ ከ30 ዓመታት በኋላ በኢኮኖሚና በቴክኖሎጂ የላቀ ደረጃ ትደርሳለች-ባለሙያዎች

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 21/2013 ( ኢዜአ) ኢትዮጵያ እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ2050 በኢኮኖሚና በቴክኖሎጂ የላቀ ደረጃ ላይ እንደምትደርስ የኢኮኖሚ ባለሙያዎች ገለጹ፡፡

የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ ወደ አዲስ ምዕራፍ የሚያሸጋግር ስትራቴጂ የያዘ ሪፖርት በኢትዮጵያውያንና በትውልደ ኢትዮጵያውን አማካኝነት ይፋ ተደርጓል፡፡

በፓናሉ የተሳተፉ 11 ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን እንዲሁም ሌሎች ባለሙያዎች አገሪቱ ብታተኩርባቸው ውጤታማ ትሆናለች ያሏቸውን ዘርፎች በመለየት መልካም አጋጣሚዎችንና ተግዳሮቶችን ለማሳየት ሞክረዋል፡፡

ከተለያዩ የትምህርት ዘርፎች በተውጣጡት ገለልተኛ ባለሙያዎች ይፋ የሆነው ሪፖርት በኢኮኖሚክስ ፣በህብረተሰብ ጤና ፣ በስታስትስቲክ ፣በትምህርት፣በስነ ህዝብ፣በቴክኖሎጂና በከተማ ልማት ዕቅድ ላይ ያተኮረ ነው ፡፡

ባለፈው ዓመት የተቋቋመው ''የሰማያዊ ሪባን'' ፓናል አገሪቱ ሊገጥሟት የሚችሉትን ፈተናዎችና ያሏትን መልካም ዕድሎች በተመለከተ በአዲስ አበባ ተወያይቷል፡፡

በዚህም የአገሪቱ የሕዝብ ብዛት ስብጥርን በተመለከተ ያላትን መልካም አጋጣሚ፣ የኢኮኖሚ ብልፅግና ፣የምግብ ዋስትና መረጋገጥ፣የትራንስፖርት መሰረተ ልማት ግንባታ፣ የፆታ እኩልነት ቀጣይ ማረፊያዎች በስፋት ዳሷል፡፡

የሪፖርቱ ማዕከላዊ ማጠንጠኛ የሕዝብ ቁጥር ለውጥ ሲሆን፤ፈጣን ከተሜነት፣ የውኃ-ምግብና-ኃይል አቅርቦት ፣የኢኮኖሚ ዕድገት፣የትራንስፖርትና የገጠር ልማት፣የተቋማትና የሲቪክ ማህበረሰብ ልማትና የፆታ እኩልነትን በመዳሰስ መፍትሄዎች ቀርበዋል፡፡

ሪፖርቱ የመንግሥትን የ10 ዓመት የልማት ዕቅድና መካከለኛ ገቢ ካላቸው አገሮች ተርታ በመሰለፍ የአፍሪካ መሪ ለመሆን የያዘችውን ትልም በመንተራስ  እንደተዘጋጀም ተገልጿል፡፡

የኢትዮጵያ 2050 ስቲሪንግ ኮሚቴ ምክትል ሊቀመንበር ኢንጂነር ተስፋዬ ወርቅነህ እንደተናገሩት "የኢትዮጵያ እኤአ2050 ኢኒሼቲቭን ስንጀምር ዋነኛ ግባችን የቴክኒካል ኤክስፐርት ቡድን በማዋቀር በሙያቸው ለአገሪቱ ልማት የበኩላቸውን ድርሻ እንዲወጡ ማስቻል ነው፡፡"

"የዚህ ዓይነት ቡድን መምራት ትልቅ ዕድል ነው፣የኤክስፐርቶቹ የትኩረት አቅጣጫ አገሪቱ እኤአ በ2050 የሚገጥማትን የሕዝብ ቁጥር ማሻቀብ ተከትሎ መልካም አጋጣሚዎችን ለልማት የምታውልበትን አቅጣጫ ማሳየት ነው ብለዋል።

አገሪቱ በተጠቀሰው ወቅት ይህንን ማሳካት ካልቻለች፤ መልካም ዕድሏን በማጣት ፈተና ላይ ትወድቃለች "በማለት የፓናሉ ሊቀመንበር ዶክተር ደብረወርቅ ዘውዴ ተናግረዋል፡፡

"ሪፓርቱ ለባለድርሻ አካላት መረጃ ለመስጠትና ተነሳሽነታቸውን ለማሳደግ ይጠቅማል፤ ከነዚህ መካከል የኢትዮጵያ መንግሥት፣የፖለቲካ ፓርቲዎች፣መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጀቶች፣ የግሉ ዘርፍና የልማት አጋሮች ይገኙበታል ብለዋል፡፡

ይህ ዶክመንት ቋሚ ማህደር በመሆን አገርን ለማሳደግና አዳዲስ ሐሳቦችን፣ስትራቴጂዎችንና ምክረ ሃሳቦችን ሥራ ላይ ለማዋል ያገለግላል" በማለትም ተናግረዋል፡፡

በውይይቱ የተሰባሰቡ ግኝቶችን በማጠቃለል ሪፖርት እንደሚያቀርብ ተነግሯል፡፡

ዶክተር ደብረወርቅ ያሳተሙትን የመጀመሪያውን ሪፖርት ለኢትዮጵያ መንግሥት ማስረከባቸውም ተገልጿል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም