አየር መንገዱ ''የአፍሪካ ምርጥ የጭነት አየር መንገድ'' ተብሎ ተመረጠ - ኢዜአ አማርኛ
አየር መንገዱ ''የአፍሪካ ምርጥ የጭነት አየር መንገድ'' ተብሎ ተመረጠ
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 21/2013 ( ኢዜአ) የኢትዮጵያ አየር መንገድ የ2020 ''የአፍሪካ ምርጥ የጭነት አየር መንገድ'' ተብሎ መመረጡን አስታወቀ፡፡
የአየር መንገዱ የጭነትና የሎጀስቲክ አገልግሎት በአፍሪካ ያለው መዳረሻ ከፍተኛ ሲሆን፣በተደጋጋሚ ''ምርጥ የጭነት አየር መንገድ'' በመባል አሸንፏል፡፡
አየር መንገዱ በጭነት አገልግሎቱ እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር የ2020 ''የአፍሪካ ምርጥ የጭነት አየር መንገድ'' ተብሎ በመመረጥ ተሸላሚ ሆኗል፡፡
አየር መንገዱ በዘርፉ በአህጉሪቱ የሚሰጠው አገልግሎት የላቀ መሆኑም ተገልጿል፡፡
ሽልማቱን የተቀበሉት የኢትዮጵያ አየር መንገድ የጭነትና የሎጀስቲክ አገልግሎት ኃላፊ አቶ ፍፁም አባዲ ባስተላለፉት መልዕከት "የአፍሪካ ምርጥ የጭነት አየር መንገድ ተብለን በመመረጣችን በጣም ደስተኞች ነን" ብለዋል፡፡
አየር መንገዱ የአቪዬሽን ኢንዱስትሪው ፈተና ላይ በሆነበት በዚህ ወቅት ለሽልማቱ መመረጡ ጥንካሬውን እንደሚያሳይም ተናግረዋል፡፡
''የሰራተኞቻችን ጥንካሬ፣ዘመናዊ አውሮፕላኖቻችንና ደረጃውን የጠበቀው መሰረተ ልማታችን በብቃት እንድንቀሳቀስ አስችሎናል ያሉን ኃላፊዎችም ከወቅቱ ጋር በመራመድ የሚሰጡት አመራር የኮቪድ 19 ወረርሽኘን ተቋቁመን ስኬት እንድናስመዘገብ አስችለውናል''ብለዋል፡፡
አየር መንገዱ ለሽልማቱ በመመረጡ ሥራቸውን በብቃት ለማከናወን እንደሚያነሳሳቸው ኃላፊው ገልጸዋል፡፡
”የኢትዮጵያ አየር መንገድ የጭነትና የሎጀስቲክ አገልግሎት ኮቪድ 19 ከተከሰተ አንስቶ እጅግ አስፈላጊ የሆኑ የሕክምና ቁሳቁስን በመላው አፍሪካና ወደ ተቀረው ዓለም በማጓጓዝ ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ አጋርነቱን በሚገባ አሳይቷል" ሲሉም ተናግረዋል፡፡
የኢትዮጵያ አየር መንገድ በአፍሪካ በግንባር ቀደምነት ከሚጠቀሱ አየር መንገዶች አንዱ መሆኑ ይታወቃል፡፡