ቀጥታ፡

የሲዳማ ክልል የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ተመሠረተ

ሀዋሳ፤ ጥቅምት 21/2013(ኢዜአ) የሲዳማ ክልል የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ሰባት አባላት ያሉት የሥራ አስፈጻሚ ቦርድ በመምረጥ ተመሠረተ። 

ጉባኤው የተመሰረተው የኢትዮጵያ ሀይማኖት ተቋማት ጉባኤ  በሀዋሳ ከተማ በሠላም ግንባታ ዙሪያ  ለሁለት ቀናት ባዘጋጀው የምክክር መድረክ ላይ ነው።

የተመሠረተው  ጉባኤ የቦርድ ሰብሳቢ ሆነው የተመረጡት ወንጌላዊ ተክሉ ዳኮሌ የኢትዮጵያ ሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ በአዲስ መልክ በተደራጀው ክልል ጉባኤው እንዲመሠረት በማድረጉ ምስጋና አቅርበዋል፡፡

በኢትዮጵያ የሀይማኖት ተቋማት ጉባኤ የተዘጋጀው መድረክ የሲዳማ ክልል የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ የሚጠበቅበትን ሀላፊነት በአግባቡ መወጣት እንዲችል እንደሚያግዘው ተናግረዋል።

ጉባኤው በሃገር ሠላምና ልማት ጉዳይ ከመንግስት ጎን በመሆን እንደሚሠራም ነው ያስታወቁት፡፡

የደቡብ ክልል የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ጽህፈት ቤት ለሲዳማ ክልል የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ የስራ መነሻ እንዲረዳውና አንድነትን ለመግለጽ  የ20 ሺህ ብር ስጦታ አበርክቷል፡፡

የጽህፈት ቤቱ አስተባባሪ መጋቢ ተሰማ ታደሰ ባስተላለፉት መልዕክት ሃገራችን ከፊት የሰነቀችው ትልቅ የልማትና የተስፋ ስንቅ ውጤታማ እንዲሆን ሠላምን መጠበቅ ይገባናል ብለዋል፡፡

ለዚህም በተለይ የሃይማኖት አባቶችና ተቋማት ከየትኛውም ጉዳይ በላይ ስለሠላም፣ አንድነት፣ አብሮነትና ወንድማማችነት ቅድሚያ ሰጥተው እንዲሰብኩና ከህዝቡ ጋር ጠንካራ ግንኙነት እንዲኖራቸው መሥራት እንደሚጠበቅባቸው ተናግረዋል፡፡

የሁለቱ ክልሎች የሀይማኖት ተቋማት ጉባኤ ለሃገር ሠላምና ልማት በጋራ በመስራት የድርሻቸውን እንደሚወጡም ገልጸዋል።

ከመድረኩ ተሳታፊዎች መካከል የኢትዮጵያ ወንጌላዊት ቤተ ክርስቲያን መካነ ኢየሱስ ማዕከላዊ ደቡብ ሲኖዶስ ምክትል ፕሬዝዳንት ቄስ አብርሃም ቱላ ለሃገር ሠላምና አንድነት ከዕምነት አባቶችና ተቋማት ብዙ እንደሚጠበቅ ተናግረዋል፡፡

በየቤተ ዕምነቱ ችግር የሚፈጥሩና የህዝብን ሠላም የሚያውኩ አገልጋዮች በየዕምነት ተቋማቱ የሚጠየቁበት አሰራር መዘርጋት እንዳለበትና በህግም ተጠያቂ መሆን እንዳለባቸውም ጠቁመዋል።

ከሲዳማ እስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት የመጡት አቶ ኡመር ሁሴን በበኩላቸው በሃይማኖት ቢለያዩም በሃገር ጉዳይ አንድ መሆናቸውን ገልጸዋል።

በሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ዕውቅና ያልተሰጣቸው ነገር ግን ተከታይ ያላቸው ቤተዕምነቶች ጉዳያቸው ታይቶ ዕውቅና እንዲያገኙ ማድረግ እንደሚገባም ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ጠቅላይ ጸሐፊ ሊቀ ትጉሐን ቀሲስ ታጋይ ታደለ እንዳሉት የኢትዮጵያ ሀይማኖት ተቋማት ጉባኤ የተመሰረተው በሰባት የዕምነት ተቋማት ነው።

ሌሎች ተቋማት ዕውቅና እንዲያገኙ ለማድረግ በጉባኤው ደንብና መመሪያ መሰረት እንደሚታይ ገልጸዋል።

በተጨማሪ አባልነት ለመታቀፍ በርካታ ጥያቄዎች እንዳሉ ያነሱት ጠቅላይ ጸሐፊው፤ ጥንቃቄ የታከለበት ጥናት ላይ ተመሥርቶ ለመመለስ እየተሠራ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

አማኝና ለዕምነቱ ቀናኢ የሆነ ህዝብ ያላት ሀገር ወንድማማችነት ላልቶ የጠብና ግጭት ወሬ መስማት እንዲያበቃም እያንዳንዱ የሃይማኖት ተቋም ለሠላም ዘብ መቆምና ትኩረት ሰጥቶ መስራት እንዳለበትም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም