ቀጥታ፡

በህዳሴ ግድብ ዙሪያ በጫና የኢትዮጵያን አቋም ለማስቀየር መሞከር ዲፕሎማሲያዊ መርህ የለውም... ምሁራን

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 21/2013 ( ኢዜአ) በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ዙሪያ በጫና የኢትዮጵያን አቋም ለማስቀየር መሞከር ዲፕሎማሲያዊ መርህ የሌለው መሆኑን ኢዜአ ያነጋገራቸው ምሁራን ገለጹ።

በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የውሃ አሞላልና አለቃቀቅ ዙሪያ ኢትዮጵያ፣ ግብጽና ሱዳን የሚያካሂዱት ድርድር እስካሁን መቋጫ አላገኘም።

ድርድሩ ለአፍሪካ ችግሮች አፍሪካዊ መፍትሄ በሚለው መርህ መሰረት በአፍሪካ ህብረት አደራዳሪነት በመካሄድ ላይ ይገኛል።

አሜሪካ ግድቡን በውሃ የመሙላትና የፍተሻ ስራውን የመሞከር ሂደት ሶስቱ አገሮች ስምምነት ላይ ሳይደርሱ መከናወን የለበትም የሚል አቋም መያዟም ይታወሳል።

ኢትዮጵያ በተፈጥሮ ሃብቷ የመልማት መብቷን ማንም ሊነጥቃት እንደማይችል የግድቡን የመጀመሪያ ዙር የውሃ ሙሌት በማከናወን አረጋግጣለች።

በሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርስቲ የዲፕሎማሲና አለምአቀፍ ግንኙነት መምህር እንዳለ ንጉሴ እንደሚሉት በህዳሴ ግድብ ድርድር የኢትዮጵያ አቋም ግልጽና የማያሻማ ነው።

የግድቡ የመጀመሪያውን ዙር መሞላቱ መሰረታዊ መሆኑን ገልጸው፤ ከዚህ በኋላ  ኢትዮጵያ አሳሪ ስምምነት ውስጥ እንድትገባ የሚያስገድዳት ነገር የለም፤ ኢትዮጵያ አሁን የያዘችው መንገድ እጅግ ትክክለኛና አዋጭ ነው ብለዋል።

በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት የውሃ ምህንድስና ትምህርት ክፍል ረዳት ፕሮፌሰር ዶክተር ቴድሮስ አሰፋ እንዳሉትም ኢትዮጵያ በያዘችው አቋም ዲፕሎማሲያዊ ጥረቷን መቀጠል ይኖርባታል።

የአገሪቷ አቋም ግልጽና ተቀባይነት ያለው መሆኑን በመግለጽ፤ መንግስትም በአለምአቀፍ መርሆ መሰረት ያንን የማስተግበርና የማስቀጠል ሃላፊነት እንዳለበት ነው የጠቀሱት።

ኢትዮጵያ አሜሪካን ጨምሮ ከሁሉም የአለም አገሮች ጋር ጥሩ የሚባል ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት እንዳላትም ምሁራኑ ገልጸዋል።

አሁን አሜሪካን እየመሩ ባሉት ፕሬዚዳንት ተለዋዋጭ አቋም ምክንያት ኢትዮጵያ ከአሜሪካ ጋር ያላት ግንኙነት የማይሻክር መሆኑንም ተናግረዋል።

ከአገራዊ ለውጡ በኋላ አለም ለኢትዮጵያ ያለው አመለካከትና ክብር ከፍ ማለቱን ያስታወሱት ምሁራኑ የግድቡ የመጀመሪያ ዙር የውሃ ሙሌት ኢትዮጵያ ለቆመችለት መርህ ያላትን ታማኝነት ያረጋገጠ ነው ብለዋል።

አለም በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት ከፍተኛ ጫና ውስጥ እየገባ ባለበት ጊዜ ኢትዮጵያ አረንጓዴ አሻራን በተሻለ በመተግበር ለሌሎች ተምሳሌት መሆኗ ሌላው የአገሪቷ የዲፕሎማሲ ከፍታ ማሳያ መሆኑንም መምህር እንዳለ ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ በራሷ አቅም በራሷ የተፈጥሮ ሃብት በምትገነባው የልማት ፕሮጀክት ልትመሰገንና ዕውቅና ሊሰጣት ሲገባ እንደ ጠላት መታየቷም በየትኛውም መመዘኛ ትክክል አይደለም ነው ያሉት።

ኢትዮጵያ ከታችኞቹ የአባይ ተፋሰስ አገሮችም ሆነ ከአለም አቀፉ ማህበረተሰብ ጋር ያላትን ዲፕሎማሲያዊ ወዳጅነት የበለጠ በማጠናከር ግንባታውን ማጠናቀቅ እንዳለባትም ጠቁመዋል።

ዶክተር ቴድሮስ አሰፋም ኢትዮጵያ ያላትን የተፈጥሮ ሃብት በራሷ አቅም የማልማትና የመጠቀም መብቷን አጠናክራ መቀጠል አለባት ነው ያሉት።

ኢትዮጵያ ማድረግ ያለባት ብቸኛው አማራጭ ሃብቷን ፍትሃዊና ምክንያታዊ በሆነ መልኩ መጠቀም መሆኑን ገልጸው፤ በዚህ አቋም እስከመጨረሻው ድረስ ሊገፋበት ይገባል  ሲሉም ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ ከምንም በላይ ውስጣዊ አንድነቷን በማስጠበቅ ለሉአላዊነቷ ዜጎቿ በጋራ መቆም እንዳለባቸውም መምህር እንዳለ ገልጸዋል።

በአውሮፓዊያኑ 2015 ኢትዮጵያ ግብጽና ሱዳን በመሪዎቻቸው ደረጃ የተፈራረሙት የመርህ ስምምነት ኢትዮጵያን የሚጠቅም እንጂ የሚጎዳ ባለመሆኑ ከግድቡ ግንባታ ጎን ለጎን ዲፕሎማሲውን ማጠናከርም ያስፈልጋል ብለዋል ምሁራኑ።

የግድቡ አጠቃላይ ግንባታ አሁን ላይ 76 በመቶ ላይ የደረሰ ሲሆን የመጀመሪያው ዙር 4 ነጥብ 9 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ውሃም እንዲይዝ ተደርጓል።

በተያዘው በጀት ዓመት አጋማሽ የግድቡ ሁለት ተርባይኖች ሃይል የማመንጨት የሙከራ ስራ እንደሚጀመርም ይጠበቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም