ቀጥታ፡

የላልይበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት ከነገ ጀምሮ ጀምሮ ለጎብኚዎች ክፍት ይደረጋሉ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 21/2013 ( ኢዜአ) የላልይበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት ከነገ ጀምሮ ለጎብኚዎች ክፍት እንደሚደረጉ ቱሪዝም ኢትዮጵያ አስታወቀ።


ቱሪዝም ኢትዮጵያ በአማራ ክልል የላልይበላ ከተማ በቱሪዝም ዘርፍ ለተሰማሩ ባለድርሻ አካላት በጎብኚዎች ደህንነት አጠባበቅ፣ ለቱሪስት መረጃ አሰጣጥና በአገር አቀፍ የቱሪዝም መለያ /ብራንድ/ ዙሪያ ስልጠና ሰጥቷል።

ስልጠናው የተሰጠው ከጎንደር፣ ባህርዳር፣ ላሊበላና ደባርቅ አካባቢ ለተወጣጡ ከ600 በላይ አስጎብኚዎች፣ የሆቴል ባለቤቶች፣ ድጋፍ ሰጪዎችና የደህንነት ጠባቂዎች ነው።

የቱሪዝም ኢትዮጵያ ዋና ዳይሬክተር ስለሺ ግርማ እንዳሉት የላልይበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት ከነገ ጀምሮ ለጎብኚዎች ክፍት ይደረጋሉ።

ላልይበላ ለጎብኝዎች ክፍት መደረጉን ተከትሎ የተለያዩ ከፍተኛ የመንግስት የስራ ሃላፊዎች የሚገኙበት የተለያዩ ዝግጅቶች ያሉበት መርሃ ግብር ይከናወናል።

በአማራ ክልል የጎንደር ቤተመንግሥት፣ ጢስ አባይ እና የሰሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ ከጥቅምት 15 ቀን 2013 ዓ.ም ጀምሮ ለጎብኚዎች ክፍት ተደርገዋል።

በአማራ ክልልና በሌሎች የኢትዮጵያ ክፍሎች የሚገኙ የቱሪዝም መዳረሻዎች እየተከፈቱ የሚገኙት የኮቪድ-19 ወረርሽኝ መመሪያን በተከተለ መልኩ መሆኑንና አስፈላጊው ጥንቃቄ እንደሚደረግም አመልክተዋል።

የኮቪድ-19 ወረርሽኝ የቱሪዝም ዘርፉን ክፉኛ እንደጎዳውና በዚህም ምክንያት በዘርፉ ተሰማርተው የነበሩ ድርጅቶች እና ግለሰቦች ያለ ስራ ለረጅም ጊዜያት እንዲቀመጡ መገደዳቸውን ዋና ዳይሬክተሩ ገልጸዋል።

በአገር ደረጃም ከቱሪዝም ዘርፍ ለማግኘት የታቀደው ገቢ ሳይሳካ መቅረቱን ነው የተናገሩት።

በአሁኑ ጊዜ ግን ኮቪድ-19 ወረርሽኝን ለመከላከል አስፈላጊውን ጥንቃቄ በማድረግ ዘርፉን ለማስጀመር ጥረት እየተደረገ እንደሚገኝም አስረድተዋል።

ለዚህም በቱሪዝም እንቅስቃሴው ላይ ግንባር ቀደም ተዋናይ ለሆኑ አካላት ስለ በሽታው መከላከል ግንዛቤ የመፍጠር ስራ በመሰራት ላይ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

አስጎብኚዎችም ቱሪስቶች ወደ አካባቢያቸው በሚመጡበት ወቅት ለደህንነታቸው ቅድሚያ መስጠት እንደሚገባቸው አሳስበዋል።

አስጎብኚዎች በአካባቢያቸው የሚገኙ ቅርሶችና መስህቦችን ከማስጎብኘት በተጨማሪ ኢትዮጵያ በሰው ዘር መገኛ፣ ጥንታዊ ባህል ያላት፣ የቡና መገኛና በሌሎችም ቀደምት ሀገር መሆኗን ማስተዋወቅ እንደሚገባቸው ነው አቶ ስለሺ ያስረዱት።

በአጠቃላይ የቱሪዝም ፍሰቱን ወደ ቀድሞው እንቅስቃሴ ለመመለስ የጎብኚዎችን ደህንነት ማስጠበቅ ላይ ትኩረት ተደርጎ እንደሚሰራ አመልክተዋል።

የስልጠናው ተሳታፊዎችም የደህንነት መጠበቂያ ዘዴዎችን ማወቃቸው ወደ ፊት በሚሰሩት ስራ ላይ አዎንታዊ ሚና እንደሚኖረው ተናግረዋል።

ጎብኚዎች ወደ አካባቢያቸው በሚመጡበት ጊዜም ማስክ መጠቀም፣ የእጅ ጓንት ማድረግ እና ጎብኚዎች ሳኒታይዘር እንዲጠቀሙ ማድረግ የመጀመሪያ ተግባራቸው እንደሚሆንም ጠቁመዋል።

በጥንቃቄ እና በመልካም መስተንግዶ ከዘርፉ ያጡትን ገቢ ለማካካስ ጠንክረው እንደሚሰሩም ነው የገለጹት።

ለቱሪዝም ዘርፍ ተዋናዮች ተመሳሳይ ስልጠና ከዚህ በፊት በሐረር እና አክሱም መሰጠቱን ከቱሪዝም ኢትዮጵያ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም