በመዲናዋ የክረምት የበጎ ፈቃድ ተግባራት ላይ ለተሳተፉ አካላት እውቅና ተሰጠ

106

አዲስ አበባ ጥቅምት 20/2013 (ኢዜአ) በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በክረምት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ላይ ለተሳተፉ አካላት ዛሬ እውቅና ተሰጣቸው። 

የአስተዳደሩ የወጣቶችና በጎ ፍቃድ ማስተባበሪያ ቢሮ ''በጎ ፍቃደኝነት ለማህበራዊ ልማት'' በሚል እሳቤ እውቅናውን የሰጠ ሲሆን፣ የበጋ የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ማስጀመሪያ መርሃ ግብርም ይፋ ሆኗል።

የቢሮው ኃላፊ አቶ አብርሃም ታደሰ በዚሁ ወቅት እንደገለጹት፣በክረምት የበጎ ፍቃድ አገልግሎትን ከእቅድ በላይ ተሳክቷል።

''ለዚህም ስኬት የክረምት የበጎ ፍቃድ ተግባር በተደራጀና በተቀናጀ መንገድ በመመራቱና የበርካታ ቅን ልቦች አስተዋጽኦ ታክሎበት ነው'' ብለዋል።

በመዲናዋ ከሰኔ 2012  እስከ መስከረም ወር 2013 ለተከታታይ አራት ወራት በተካሄደው መርሃ ግብር 1 ነጥብ 9 ሚሊዮን በጎ ፍቃደኞች ተሳተፍውበታል።

በአገልግሎቱም  ከ3 ነጥብ 6 ሚሊዮን በላይ ነዋሪዎችን ተጠቃሚ መሆናቸውን ኃላፊው አስታውቀዋል።

በዚህም 566 ሚሊዮን ብር በላይ የሚሆን የበጎ ፍቃድ መስጠት ተችሏል ያሉት አቶ አብርሃም፤ ከዚህም ውስጥ 241 ሚሊዮን በላይ የሚሆነው በአገልግሎት፣ቀሪው ደግሞ በሃብት ማሰባሰብ እንደተገኘ አስረድተዋል።

በመርሃ ግብሩ የኮሮና ቫይረስ መከላከል ፣ የቤት እድሳት፣ ችግኝ ተከላ ፣የመንገድ ትራፊክ፣የደም ልገሳ፣ ሰብዓዊ አገልግሎት፣የሙያ በጎ ፍቃድና ሌሎችም ተግባራት ተከናውነበታል።

በቀጣይም እስከ ግንቦት ወር ድረስ የበጋ የበጎ ፍቃድ አገልግሎት እንደሚካሄድ ኃላፊው ገልጸዋል።

የሴቶች፣ ህጻናትና ወጣቶች ሚኒስትር ወይዘሮ ፊልሰን አብደላ በዚሁ ወቅት እንደተናገሩት ወደ ተሻለ ብልጽግና አገርንና ሕዝብን ለማሻገር የበጎነት ሥራ መጠናከር አለበት።

በቀጣይም ሚኒስቴሩ የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ለማስፋፋት ከወጣቶች ጋር እየሰራ ነው ብለዋል።

በመርሃ ግብሩ የተሳተፉ መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት፣ ማህበራት፣ ክፍለ ከተሞች እውቅና ተሰቷቸዋል።

የአስተዳደሩ ከንቲባ ጽህፈት ቤትና የሴቶች፣ ህጻናትና ወጣቶች ጉዳይ ሚኒስቴር በልዩ ተሸላሚነት እውቅና አግኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም