ቀጥታ፡

የአሜሪካ ፕሬዚዳንት የጥፋት መልዕክት የተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች ነዋሪዎችና ምክር ቤት አባላት አወገዙ

ፍቼ/ድሬዳዋ/ደብረማርቆስ/መተማ /ሶዶ/ሀዋሳ / ጥቅምት 20/ 2013 (ኢዜአ) የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን አስመልክተው ያስተላለፉት የጥፋት መልዕክት በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች የሚገኙ ነዋሪዎችና ምክር ቤት አባላት አወገዙ። 

የአሮሚያ ፣ አማራ፣ ደቡብ ክልሎችና ድሬዳዋ አስተዳደር  ነዋሪዎች የፕሬዚዳንቱን  መልዕክት ያወገዙት ጉዳዩን አስመልክቶ ለኢዜአ  በሰጡት አስተያየት ነው።

ከፍቼ ከተማ ነዋሪዎች መካከል የህግ ባለሙያ የሆኑት አቶ ኢሳያስ ጥበቡ እንዳሉት የዶናልድ ትራምፕ ጣልቃ በመግባት ለአንድ ወገን ያደላ ተንኳሽ ንግግር ሀላፊነት የጎደለው  አስተሳሰብ ነው።

አሁንም ግብፅና ኢትዮጰያን በሚያስማማና ሚዛናዊነትን በጠበቀ መልኩ ንግግራቸውን ማረም እንዳለባቸው በማመልከት የጥፋት መለዕክታቸውን  በመቃወም አውግዘዋል፡፡

የፍቼ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ርዕሰ መምህር በላይ ወልደጻዲቅ በበኩላቸው  ፕሬዚዳንቱ  የተናገሩት ተንኳሽ ቃል ኢትዮጰያውንን የበለጠ እንደሚያጠናክርና ለግድቡ የሚያደርጉትን ድጋፍም እንዲቀጥሉ የሚያነሳሳ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በኦሮሚያ የሰሜን ሸዋ ዞን የህዳሴ ግድቡ  የህዝብ ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት ተጠሪ  አቶ  ቂናጤ ጫላ ፕሬዚዳንቱ የአንድን ሉአላዊ ሀገር ጥቅም ወደኋላ በማለት ያወጡት ቃል የአፍሪካና ለጥቁር ህዝቦች ያላቸውን ዝቅተኛ አመለካከት ያሳያል ብለዋል፡፡

በዞኑ ባለፉት ዓመታት ከህዝብ ለግድቡ ግንባታ ከ27 ሚሊዮን ብር በላይ መሰብሰቡን አመልከተው አሁንም በእልህና በቁጭት ድጋፋቸውን አጠናክረው የሚቀጥሉበት ሁኔታ እንደተፈጠረ  አስረድተዋል።

በሌላ በኩል  በምዕራብ ጎንደር ዞን የገንዳውሃ ከተማ ነዋሪዎች መካከል ወጣት ፈረደ መንግስቴ በሰጠው አሰተያየት የፕሬዚዳንቱ ንግግር ለአንዲት ልዕለ ሃያል ሀገር መንግስትና መሪ የማይመጥን መሆኑን ተናግራል።

ግድቡ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ዋልታ ከመሆኑ ባሻገር የሉዓላዊነት መገለጫ በመሆኑ አስፈላጊውን የገንዘብ ድጋፍ ለማድረግ መነሳሳቱን ገልጿል፡፡

ሌላኛው የከተማዋ ነዋሪ አቶ ገበያው ዋሴ በበኩላቸው የፕሬዚዳንቱ ንግግር ህዝባዊ ትብብርን በማጠናከር ግድቡ በፍጥነት እንዲጠናቀቅ የሚያደርግ ነው ብለዋል።

 ከመንግስት ጎን በመሰለፍ ጠላትን ለማሳፈር የድርሻቸውን እንደሚወጡም ተናግረዋል።

"ተፎካካሪ ፓርቲዎችም በሀገራቸው ጉዳይ የማይደራደሩ መሆናቸውን ማሳየት የሚገባቸው ጊዜ አሁን ነው" ያሉት ደግሞ በከተማዋ የሆቴል ባለቤት ወይዘሮ መዓዛ አረጋይ ናቸው፡፡

ከዚህ በፊት የ25ሺህ ብር ቦንድ መግዛታቸውን አስታውሰው ዘንድሮ ተመላሽ ከሚሆንን 5ሺህ ብር ላይ በመጨመር የ10ሺህ ብር ቦንድ  አሁንም ለመግዛት መወሰናቸውን ተናግረዋል፡፡

የደብረ ማርቆስ ከተማ  አቶ ምትኩ ነጋ የአባይ ጉዳይ የህልውናችን ጉዳይ መሆኑን ያልተረዱ ግለሰቦች በገንዘብ ለማታለል ቢሞክሩም ጠንካራ አቋም ያለው ህዝብ ስለሆንን አንታለልም ብለዋል።

የዘሁ ከተማ ነዋሪው ወጣት ዳንኤል ልኡል እንዳለው የዶናልድ ትራምፕ የጥፋት መልዕክት የኢትዮጵያ ህዝብ ህልውና ላይ  ያነጣጠረ ነው።  

በመንገድ ላይ ንግድ ስራ ቢሰማራም ባለፈው ክረምት ከግድቡ ውሃ ሙሌት ጋር ተያይዞ የ500  ብር ቦንድ እንደገዛ ገልጾ ተጨማሪ  ቦንድ ለመግዛት መወሰኑም ተናግሯል።

በተያያዘ ዜና  የድሬዳዋ ነዋሪዎች   የአሜሪካው ፕሬዘዳንት በግድቡ ላይ የሰጡትን አስተያየት በማውገዝ  በግድብ የሚመጣን እስከ ህይወት መስዋጥነት ለመመከት ዝግጁ መሆናቸውንም ገልጸዋል፡፡

ከነዋሪዎቹ መካከል የሶሰተኛ ዓመት  የፖለቲካ ሳይንስና አለም አቀፍ ግንኙነት ተማሪ ወርቅነህ አበበ  እንደተናገረው፤ ግድቡ የኢትዮጵያ የዕድገትና የነገ ብልጽግና ተስፋ ነው፡፡

ዜጎች ለአሜሪካው ፕሬዘዳንት አስተያየት ተገቢውን የዲፕሎማሲና የተቃውሞ ድምጽ ለአለም ማህበረሰብ ማሰማት አለባቸው ብሏል፡፡

መንግስት ግድቡ በሰመረ መንገድ እንዲጠናቀቅ ከተፋሰሱ ሀገራት ጋር የጀመራቸውን የድርድርና የውይይት ሂደት ማጠናከር እንዳለበትም ጠቁሟል።

የአሜሪካው ፕሬዘዳንት ንግግር ከሳቸው የሚጠበቅ አለመሆኑን የገለፁት ደግሞ ሐጂ ኡመር ዩሱፍ ናቸው ፡፡

ዜጎች በራሳቸው ሀብትና ላብ የገነቡትን ግድብ እንደ ተራ ድልድይ ማፍረስ ነው ብሎ ማወጅ አሳፋሪና አስነዋሪ ተግባር ነው ብለዋል፡፡

ወጣት ከድር አልይ በበኩሉ የህዳሴው ግድብ የወጣቶች የነገ መበልፀጊያ መንገድ መሆኑን ገልጾ ይህን መንገዳችንን ለማጥፋት የሚነሳብንን ጠላት ለመመከት ዝግጁ ነን ብሏል፡፡

የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሣይንስና አለም አቀፍ ግንኙነት ትምህርት ክፍል መምህር  አቶ ሱራፌል ጌታሁን  ግብጽን ለመካከለኛው ምስራቅ የፖለቲካ ትኩሳት ማርገቢያ መሣሪያነቷን ለማጠናከር ግድቡን ለድርድር ማቅረባቸው እኩይና የሚወገዝ ተግባር መሆኑን ተናግረዋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ  የህዳሴውን ግድብ ግንባታ ለማጠናቀቅ  አንድነት በይበልጥ ማጠናከር  እንደሚያስፈልግ  በወላይታ ዞን ምሁራን ተናግረዋል።

የወላይታ ሶዶ ዩኒቨርስቲ የህግ መምህር አብነት ጨመረ እንዳሉተ የግድቡ የመጀመሪያ ዙር ፍ ውሃ ሙሌት በሰኬት መጠናቀቁ  የህብረተሰቡን የነገ ተስፋ ያለመለመ ነው።

በቀጣይም የግድቡን ግንባታ ለማጠናቀቅ በጋራ መቆም የተሻለ አቅም የሚገነባ በመሆኑ አንድነታችንን በይበልጥ ማጠናከር ያሰፈልጋል ብለዋል።

የወላይታ ዞን ዓቃቤ ህግ ባለሙያ አቶ መብራቱ በለጠ በበኩላቸው በግድቡ ዙሪያ የሚደረግ ማንኛውም ውይይት ግን የሃገሪቱን ፍትሀዊ ተጠቃሚነትን የሚያረጋግጥ ሊሆን እንደሚገባ ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ በአባይ ወንዝ ላይ ያላትን የመልማት ባለቤትነት መብት ለመጋፋት የሚደረግ ማንኛውንም ጥረት እንደሚቃወሙ ግለዋል።

በዞኑ የታላቁ ህዳሴ ግድብ ህዝባዊ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ምክር ቤት ባለሙያ አቶ ዘርገነ ወይሻ በበኩላቸው በዞኑ ካለፈው ነሀሴ ወር ጀምሮ ከ236 ሺህ ብር በላይ በቦንድ ግዥ መሰብሰቡን አመልክተው የግድቡ ግንባታ ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ እስካሁን ከ200 ሚሊዮን ብር በላይ  ድጋፍ መደረጉን አውስተዋል።

የደቡብ ክልል የብሄረሰቦች ምክር ቤት አባላት በበኩላቸው  የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ሃላፊነት የጎደለው መግለጫ ኢትዮጵያውያን የጀመሩትን የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ከማጠናቀቅ እንደማገድባቸው ገልጸዋል።

ከአባላቱ መካከል አቶ አክሊሉ ወልደሚካኤል ከኢትዮጵያ የሚመነጨው የአባይ ወንዝ ለዘመናት ተገቢውን ጥቅም ሳይሰጥ መቆየቱ የሚያስቆጭ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ህዝብና መንግስት በመተባበር የግድቡን ግንባታ   እያፋጠኑ ባሉበት ሁኔታ ሰሞኑን የአሜሪካው ፕሬዚዳንት የሰጡት አስተያየት ሃላፊነት የጎደለውና ከአንድ መሪ የማይጠበቅ መሆኑን ገልጸዋል።

ኢትዮጵያዊያን የማይደራደሩበት አቋም ይዘው የጀመሩት ሃገራዊ ፕሮጀክት መሆኑን ጠላቶች ሊያውቁ ይገባል ብለዋል፡፡

ሌላ የምክር ቤቱ አባል አቶ ጀማል አማሮ በበኩላቸው  ሰሞኑን የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ያወጡት መግለጫ ከአንድ የሃገርና ከፍተኛ ሃላፊነት ካለው መሪ የማይጠበቅ ነው ብለዋል፡፡

ይህም ግድቡን ለማጠናቀቅ እየተደረገ ያለውን ድጋፍና አንድነት የሚያጠናክር እንጅ የሚያስበረግግ  እንዳልሆነ ተናግረዋል።

ዶናልድ ትራምፕ የሰነዘሩት አስተያየት ኢትዮጵያውያን በሃገር ሉዓላዊነት የማይደራደሩ መሆናቸውን ካለማወቅ ሳይሆን ለግብጽ መወገናቸውን በግልጽ ያሳየና የማይገባ መሆኑን  የገለጹት ደግሞ ሌላው የምክር ቤት አባል  አቶ ባርኮይ ኦሌቻጊ ናቸው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም