ቀጥታ፡

የአባይ ተፋሰስን በቆላ ቀርከሃ ዛፍ ለማልማት አራት ተቋማት የመግባቢያ ስምምነት ተፈራረሙ

አዲስ አበባ ጥቅምት 20/2013 (ኢዜአ) የሰላሌና የደብረማርቆስ ዩኒቨርሲቲዎች፣ የአካባቢ ደን እና የአየር ንብረት ለውጥ ኮሚሽንና የኢትዮጵያ አካባቢና የደን ምርምር ኢንስቲትዩት የአባይ ተፋሰስን በቀርከሃ ዛፍ ለማልማት የመግባቢያ ስምምነት ተፈራረሙ። 

ለልማቱ 10 ሺህ የቀርከሃ ዛፍ ችግኝ የተዘጋጀ ሲሆን በዚህ ዓመት 500 ሺህ ችግኝ ለማዘጋጀት እየተሰራ መሆኑን የአካባቢና የደን ምርምር ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አብዮት ብርሃኑ ገልፀዋል።

የአባይ ሸለቆ ብዝሃ ህይወቱ የተመናመነና የተጎዳ አካባቢ በመሆኑ ለማልማት የሚያስችል ነው ብለዋል።

ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ በደለል እንዳይሞላ ለማድረግ በአካባቢው የቀርከሃ ዛፍ መትከል የሚያስችል መሆኑንም ጠቁመዋል።

የቀርከሃ ዛፍ በረሃማነትን የሚቋቋም ተክል ከመሆኑ በተጨማሪ በስሮቹ አፈር እንዳ ይሸረሸር የማድረግ ከፍተኛ እቅም አለው ነው ያሉት።

በቶሎ የሚያድግ በመሆኑም ችግኞቹን የማባዛት ስራ እየተከናወነ ይገኛል ብለዋል።

የአካባቢ፣ የደንና የአየር ንብረት ለውጥ ኮሚሽነር ፕሮፌሰር ፍቃዱ በየነ የሰላሌና የደብረማርቆስ ዩኒቨርሲቲዎች በተፋሰስ ልማትና በአካባቢ ጥበቃ ስራ የጀመሩት ስራ ለሌሎች አርዓያ እንደሚሆን ተናግረዋል።

ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ከህብረተሰቡ ጋር በቅርበት የሚሰሩ በመሆናቸው በአካባቢ ጥበቃና በደን ልማት የሚሰሩትን ስራ ውጤታማ እንደሚያደርገውም ገልፀዋል።

ስራው አካባቢውን ከማልማት ባሻገር ለወጣቶችና ለሴቶች የስራ ዕድል ፈጠራ ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንዳለውም ጠቁመዋል።

የአባይ ተፋሰስ ልማት በአካባቢው ሕዝቦች መካከል ያለውን ትስስር የበለጠ ያጠናክራል ሲሉ የሁለቱ ዩኒቨርሲቲዎች ፕሬዚዳንቶች ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም