የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ለ"ገበታ ለሀገር" ፕሮጀክት የ1 ነጥብ 1 ቢሊዮን ብር ድጋፍ አደረገ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ለ"ገበታ ለሀገር" ፕሮጀክት የ1 ነጥብ 1 ቢሊዮን ብር ድጋፍ አደረገ
አዲስ አበባ ጥቅምት 20/2013 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ለገበታ ለሀገር ፕሮጀክት የ1 ነጥብ 1 ቢሊዮን ብር ድጋፍ አደረገ።
የባንኩ ፕሬዚዳንት አቶ አቤ ሳኖ እና የቦርድ ሊቀመንበሩ አቶ ተክለወልድ አጥናፉ ለፕሮጀክቱ ያደረጉትን የ1 ቢሊዮን 100 ሚሊዮን ብር ድጋፍ ዛሬ ለጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ አስረክበዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የሕዝብ በመሆኑ ለሕዝብ ለሚውሉ የልማት ፕሮጀክቶች ድጋፉን እያደረገ እንደሆነ ገልጸዋል።
የፋይናንስ ዘርፉ በአጠቃላይ ለ"ገበታ ለሀገር" ፕሮጀክት 1 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር ድጋፍ ማድረጉንም አስታውሰዋል።
የመንግስት ሠራተኞችና ተቋማት፣ የፋይናንስ ተቋማት፣ ዳያስፖራውና ግለሰቦች ለገበታ ለሀገር ፕሮጀክት ድጋፍ እያደረጉ መሆኑን የገለፁት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህንኑ አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጥሪ አቅርበዋል።
አገር የምትለማው የዜጎች እውቀትና ጉልበታቸው መደመር ሲችል እንደሆነ ገልፀው ይህን ማድረግ ከተቻለ በአጭር ጊዜ ወደ ብልጽግና ማማ መውጣት እንደሚቻል አክለዋል።
በገበታ ለሀገር የሚሰሩ ፕሮጀክቶች ግንባታቸው ሲካሄድም ሲጠናቀቁም ለዜጎች የስራ ዕድል የሚፈጥሩ መሆናቸውን ተናግረዋል።
የገበታ ለሀገር ፕሮጀክቶች ሲጠናቀቁ በሌሎች ክልሎችም እንደሚቀጥል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጠቁመዋል።
ትናንት በሶማሌ ክልል ባደረጉት ጉብኝት የግሉ ዘርፉ በክልሉ የተጀመሩ ፕሮጀክቶችን ለማጠናቀቅ ሌት ተቀን እየሰራ እንደሆነ ተመልክቻለሁ ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህም በኢትዮጵያ ፕሮጀክት የማጠናቀቅ ባህል እያደገ መምጣቱን እንደሚያሳይ ጠቅሰዋል።
ኅብረተሰቡ በአንዳንድ አካባቢዎች የሚታዩ የጸጥታ ስጋቶች የተጀመሩ የልማት ስራዎችን ለማደናቀፍ መሆኑን አውቆ ለሠላም ዘብ መቆም እንደሚገባውም አሳስበዋል።
የገበታ ለሀገር ፕሮጀክት የገቢ ማሰባሰቢያ መርሃ ግብር በቅርቡ በሚካሄት የእራት ፕሮግራም ይጠናቀቃልም ብለዋል።
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የቦርድ ሊቀመንበር አቶ ተክለወልድ አጥናፉ በበኩላቸው ባንኩ ከምስረታው አንስቶ በአገሪቷ በሚከናወኑ የልማት ስራዎች ድጋፉን እያደረገ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
ከሚያገኘው ትርፍ አብዛኛውን ለልማት ስራዎች በድጋፍና በብድር መልክ እንደሚያውልና የዛሬው ድጋፍም የዚሁ ማሳያ እንደሆነ ጠቅሰዋል።
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፕሬዚዳንት አቶ አቤ ሳኖ ባንኩ ለገበታ ለሀገር ፕሮጀክት ካደረገው የ1 ነጥብ 1 ቢሊዮን ብር ድጋፍ ውስጥ 571 ሚሊዮን ብር ከባንኩ ሠራተኞችና ከቦርዱ የማኔጅመንት አባላት የተሰበሰበ መሆኑንና ቀሪው ባንኩ ከራሱ ወጪ አድርጎ የሰጠው መሆኑን ገልጸዋል።
ፕሮጀክቱ ከሚያስገኘው ጥቅም አንጻር ይህንን ድጋፍ ሳይሆን እንደ ትልቅ ኢንቨስትመንት የምንቆጥረው ነው ብለዋል።
ንግድ ባንክ በአገር ልማት ስራዎች ጠንካራ ተሳትፎ እያደረገ መሆኑንና በቀጣይም ስራ አጥነትን ለመቀነስ እንደሚሰራ ገልጸዋል።
የገበታ ለሀገር ፕሮጀክት ብሔራዊ ኮሚቴ አባልና የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ ዶክተር ይናገር ደሴ ለፕሮጀክቱ የተደረገው ድጋፍ የመላው የባንክ ሠራተኛ ትልቅ ሚና ያለበት ነው ብለዋል።
ባንኮች፣ የኢንሹራንስ ድርጅቶች የሊዝ ኩባንያዎች ለገበታ ለሀገር ፕሮጀክት ድጋፍ እያደረጉ መሆኑንና በአጠቃላይ የፋይናንስ ዘርፉ ድጋፍ ትልቅ ድርሻ እንዳለው ገልፀዋል።
የፋይናንስ ዘርፉ ለገበታ ለሀገር ፕሮጀክት እያደረገ ያለውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልፀው ሌሎች አካላትም የጀመሩትን ድጋፍ እንዲቀጥሉ ጥሪ አቅርበዋል።