ቀጥታ፡

ድሬዳዋ ኢንዱስትሪ ፓርክ ለወደብ ቅርብ መሆኑ የኢንዱስትሪ ዘርፍን በፍጥነት ለማሰደግ ጉልህ ሚና ይኖረዋል---ጠቅላይ ሚኒስትር

አዲስ አበባ ጥቅምት 20/2013 (ኢዜአ) የድሬዳዋ ኢንዱስትሪ ፓርክ ለወደብ ቅርብ በመሆኑ ኢንዱስትሪ ዘርፍን በፍጥነት በማሰደግ በኩል ጉልህ ሚና እንደሚኖረው ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ ተናገሩ።

ጠቅላይ መኒስትር ዶክተር ዐቢይ  ይህን ያሉት የድሬዳዋ ኢንዱስትሪ ፓርክን በይፋ መርቀው ሥራ ባስጀመሩበት ወቅት ነው።

የድሬዳዋ ኢንዱስትሪ ፓርክ  አጠቃላይ 300 ሺህ ሄክታር መሬት ስፋት ያለው ሲሆን ከዚህም ውስጥ 150 ሄክታር መሬቱ በመጀመሪያው ዙር መልማቱ ተገልጿል።

በፓርኩ ውስጥም 15 ግዙፍ የማምረቻ ሼዶች፣ የአንድ መስኮት አገልግሎት ህንጻዎችና የመኖሪያ ቤቶች ተገንብተዋል።

የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ሳንዶካን ደበበ በዚህን ወቅት እንዳሉት፤ ፓርኩ ቆሻሻ ፍሳሾችን የሚያጣራ ዘመናዊ ቴክኖሎጂ የተገነባለት በመሆኑ ከአካባቢ ብክለት የጸዳ ነው።

በፓርኩ ውስጥ ባሉ ሁሉም ሼዶች ኢንቨስተሮች እንዲገቡም የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ከኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ጋር  በጋራ እየሰሩ መሆናቸውን ነው የተናገሩት።

የፓርኩ ወደ ሥራ መግባት የድሬዳዋ ከተማን ቀደምት የኢንዱስትሪ ማዕከልነት እንደሚመልሰው ያላቸውን እምነት በመግለጽ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ በበኩላቸው የድሬደዋ ከተማ ዘመናትን ያስቆጠረ የኢንዱስትሪና ልማት ማዕከልነት ታሪክ ያላት መሆኗን አስታውሰዋል።

"የፓርኩ መገንባትም ያላትን ታሪክ በተግባር እንድትደግፍ ያግዛታል" ብለዋል።

የድሬዳዋ ኢንዱስትሪ ፓርክ ለጅቡቲ ወደብ ቅርብ ከመሆኑም ባለፈ የኢትዮጵያ ጁቡቲ የባቡር  አገልግሎትን በቅርቡ የሚያገኝ መሆኑ ደግሞ ፓርኩን ውጤታማ ያደርገዋል ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ።

በተጨማሪ የድሬዳዋ ከተማና አካባቢዋ ነዋሪዎች በፋብሪካዎች ላይ በመስራት ረገድ ጥሩ ልምድ ያላቸው መሆኑም ፓርኩ ውጤታማነት እድል ይዞ እንደሚመጣ ጠቁመዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ በድሬዳዋ ቆይታቸው ከኢንዱስትሪ ፓርክ በተጨማሪ  በከተማዋ የተገናባና የእንስሳት ሥጋ ምርትን ለውጭ ገበያ ለማቅረብ የሚያስችል ቄራ መርቀው ከፍተዋል።

ከድሬድዋ  በቅርብ ርቀት የተገነባው ይህ ቄራ በቀን ከአንድ መቶ በላይ ግመል እና ከ3 ሺህ በላይ የበግ እና ፍየል እርድ የማከናወን አቅም አለው ተብሏል።

ቄራው በአካባቢው ያለውን ሰፊ የቁም እንስሳት ሀብት በመጠቀም የውጭ ምንዛሬ  ከማስገኘት ባለፈ  ለአካባቢው ማህበረሰብ የሥራ እድል በመፍጠር ረገድ ጉልህ ሚና እንደሚኖረው ታውቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም