ድርጅቱ አገሮች የበረሃ አንበጣን የመከላከል አቅሙ ለማሳደግ ድጋፍ እንዲያደርጉለት ጠየቀ - ኢዜአ አማርኛ
ድርጅቱ አገሮች የበረሃ አንበጣን የመከላከል አቅሙ ለማሳደግ ድጋፍ እንዲያደርጉለት ጠየቀ
አዲስ አበባ ጥቅምት 20/2013 (ኢዜአ) አገሮች ለምስራቅ አፍሪካ የበረሃ አንበጣ መከላከያ ድርጅት የሚያደርጉትን ድጋፍ እንዲያጠናክሩ የድርጅቱ ዳይሬክተርና የዘርፉ ባለሙያዎች ጠየቁ።
የዓለም የምግብና ግብርና ድርጅት መንጋው በኢትዮጵያና በሶማሊያ እስከ ታህሳስ አጋማሽ ጉዳት ሊያደርስ ይችላል ብሏል።
ድርጅቱ አንበጣ መብረር ሳይጀምር ለመቆጣጠር እንዲሰራም አሳስቧል።
እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ1962 በአዲስ አበባ ከተማ በተፈረመ ዓለም አቀፍ ስምምነት በምስራቅ አፍሪካ ተባይን ለመከላከል የተመሰረተው ድርጅት በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያን ጨምሮ ዘጠኝ አገሮችን በአባልነት ይዟል።
ድርጅቱ የበረሃ አንበጣ የሚያደርሰውን ጉዳት መከላከያና መቆጣጠሪያ መንገዶችን ለመተንበይ የተቋቋመ የነበረ ሲሆን፣ አሁን ግን ከበረሃ አንበጣ ባሻገር ሌሎች ድንበር ዘለል ተባዮችን መከላከልንም በኃላፊነቱ ውስጥ አካቷል።
ድርጅቱ በቀደሙት ዓመታት አንበጣን በመከላከል ረገድ አስተዋፅኦው የጎላ እንደነበር የዘርፉ ባለሙያዎች ያነሳሉ።
በአሁኑ ወቅት የተከሰተውን የበረሃ አንበጣ ለመቆጣጠር የቀጣናው አገሮች በትብብር መስራት እንደሚያስፈልግና ለዚህም የድርጅቱ አቅም መጠናከር እንዳለበትም ይገልፃሉ።
ዶክተር ታደለ ተፈራ የአፍሪካ ተባይ ሳይንስ ለምግብና ጤና ተቋም የኢትዮጵያ ኃላፊ እንደገለፁት ”የበረሃ አንበጣን መከላከል ካስፈለገን እኛ አገራችን ላይ ከደረሰ ጊዜ ሳይሆን፤ ሳይደርስ በፊት ከምንጩ ሄደን ነው መከላከል ያለብን። ይሄ ምንድነው የሚያሳየው የአገራት በተለይ የአጎራባች የሆኑ አገራት መተባበር እንዳለባቸው ያሳያል። ”
“የምስራቅ አፍሪካ የአንበጣ መከላከያ ድርጅት እንደውም በኢትዮጵያ መሪነት የተቋቋመ ድርጅት አለና እሱን ማጠናከር ብዙ ምርጫ ያለው ነገር አይደለማ እኛ ኢትዮያ ብቻዋን ልትወጣው የምትችል ችግር አይደለምና የእነኚህን አገሮች አንድ ላይ የመስራት ነገር ማጠናከር በጣም ወሳኝ ነገር ይመስለኛል” ያሉት የኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ አባል ዶክተር ብርሃኔ ገብረ ኪዳን ናቸው።
ድርጅቱ በበኩሉ አንበጣ በሚከሰትበት ወቅት መረጃዎችን ከሌሎች ዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር በመቀናጀት ለአገሮቹ የግብርና ሚኒስትሮች እያሳወቀ መሆኑን ይናገራል።
የድርጅቱ ዳይሬክተር ዶክተር ስቴፈን ጆካ ለኢዜአ እንዳሉት የበረሃ አንበጣ በቀጣናው አገሮች ላለፉት 20 ዓመታት አስጊ በሆነ ደረጃ አልተከሰተም።
ሆኖም ባለፈው የፈረንጆቹ ዓመት የበረሃ አንበጣ ከተከሰተ ጀምሮ ከዓለም ምግብ ፕሮግራም (FAO) በሚገኘው ተባዩን የተመለከተ መረጃ እየተተነተነ ድጋፍ እየተደረገ መሆኑንም አስረድተዋል።
ድርጅቱ አንበጣውን ለመከላከል አውሮፕላኖችን እያሰማራ ቢሆንም፤ አውሮፕላኖቹ አሮጌ በመሆናቸው ዘመናዊ ለማድረግ የአገሮች ድጋፍ ወሳኝ መሆኑን ይናገራሉ።
የድርጅቱ አቅም በባለሙያዎችና በዘመናዊ አውሮፕላን መጠናከር ጉዳቱን ለመቆጣጠር እንደሚያግዝ ዶክተር ጆካ አመልክተዋል።
አውሮፕላኖቹ ከአንበጣ በተጨማሪ ሌሎች ተባዮችን ለመከላከል እንደሚያግዙም አስረድተዋል።
አገሮች አንበጣው በእንቁላል ደረጃ እያለና መብረረ ሳይጀምር መቆጣጠር እንዳለባቸው ያሳሰቡት ዳይሬክተሩ፣ በዚህ ረገድ ኤርትራ ያከናወነችው ተግባር የሚያበረታታ መሆኑን መስክረዋል።
ኢትዮጵያ በአሁኑ ሰዓት አንበጣን ለመከላከል እያደረገች ያለችውን ተግባር የሚያበረታታ መሆኑን ገልጸው፣ ሌሎችም አገሮች ጥረታቸው ማጠናከር ይገባቸዋል ብለዋል።
የዓለም የምግብና ግብርና ድርጅት የበረሃ አንበጣ በኢትዮጵያና በሶማሊያ እንደገና እየተፈለፈለ በመሆኑ እስከ ታህሳስ ወር አጋማሽ ጉዳት ሊያደርስ እንደሚችል ሰሞኑን ባወጣው መግለጫ አስጠንቅቋል።