ቀጥታ፡

ህዝበ ሙስሊሙ ለሕዳሴው ግድብ የሚያደርገውን ተሳትፎ አጠናክሮ ይቀጥላል

አዲስ አበባ ጥቅምት 20/2013 (ኢዜአ) በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የህዝበ ሙስሊሙን ተሳትፎ ይበልጥ ለማሳደግ እንደሚሰሩ የአዲስ አበባ እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት የቦርድ አመራሮች ተናገሩ፡ የፕሬዘዳንት ትራምፕ ንግግር ለፍትሃዊው ዓለም ከንግግር የዘለለ አንዳችም ተጽእኖ ሊፈጥር እንደማይችልም ጠቁመዋል፡፡ 

የአዲስ አበባ እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት የቦርድ ሰብሳቢ አቶ አዩብ አብደላ ህዝበ ሙስሊሙ የሕዳሴው ግድብ ግንባታ ሥራ ከተጀመረ ጀምሮ እያደረገ  ያለው ድጋፍ  ከፍተኛ መሆኑንና በቀጣይም ድጋፉ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል።

ግድቡ የኢትዮጵያዊያን የህልውና ጥያቄ መሆኑና ከኢትዮጵያውያን ውጭ ማንም የሚመለከተው እንዳልሆነ የገለጹት አቶ አዩብ ፣ በቅርቡ የአሜሪካው  ፕሬዚዳንት  ግድቡን  አስመልክቶ ያስተላለፉት መልዕክት ተገቢነት የሌለውና ኢትዮጵያዊያንን ያስቆጣ መሆኑን ገልጸዋል።   

ኢትዮጵያዊያን በህዳሴው ግድብ ዙሪያ የሚነሱ አፍራሽ አመለካከቶችን እንደ ውጫሌ ስምምነት በግድ ለማስማማት የተደረገ አድርገው እንደሚቆጥሩትም ነው የተናገሩት፡፡

"የፕሬዚዳንቱ ስሜታዊ ንግግር ለሕዳሴው ግድባችን ድጋፋችንን የበለጠ እንድናጠናክር እልህ ውስጥ አስገብቶናል" ሲሉም ነው አቶ አዩብ የገለጹት፡፡

ኢትዮጵያዊን በተለይ መላው የሙስሊሙ ህዝብ ለግድቡ ግንባታ እያደረገ ያለውን ድጋፍ በተሻለ አጠናክሮ እንዲቀጠል የበኩላቸውን እገዛ እንደሚያደርጉም ተናግረዋል ።

የአዲስ አበባ እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት ምክትል የቦርድ ሰብሳቢ ኡስታዝ ሙሃመድ አባተ በበኩላቸው ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ኢትዮጵያኖች  ዘር፣  ሃይማኖት ፣ የፖለቲካ አስተሳሰብም ሆነ ምንም አይነት ልዩነቶች  ሳያግዷቸው ከድህነታቸው  ቆጥበው እየገነቡት ያለና የህልውናቸው መሰረት መሆኑን ተናግረዋል።

"የኢትየጵያን ህዝብ ያለልዩነት ያስተሳሰረና እንደአንድ ሆነው እንዲናገሩ ያደረገ  ጉዳይ ቢኖር የህዳሴው ግድብ ነው" ሲሉም ኡስታዝ ሙሀመድ አባተ ተናግረዋል፡፡

ሰሞኑን የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ የአሜሪካንን ህዝብ ሳይሆን የራሳቸውን ስብዕና በሚያሳይ መልኩ ስለሕዳሴው ግድብ ያደረጉት ንግግር ወገንተኝነትን ያሳየ መሆኑን ጠቁመው፣ ንግግራቸው የኢትዮጵያ  ህዝብ አንድነቱን በማጠናከር  ግድቡን  ለማጠናቀቅ ዳግም ያነሳሳው መሆኑንን ገልጸዋል።

ፕሬዚዳንቱ ኃላፊነት የጎደለውና ቀውስ ሊያስከትል የሚችል ንግግድ ማድረጋቸው አሳዛኝ መሆኑንም ኡስታዝ ሙሀመድ ገልጸዋል።

የሕዳሴው ግድብ የኢትዮጵያኖች ህልውና መሆኑንና ማንም ኢትዮጵያዊ በህልውናው ላይ እንደማይደራደርም ኡስታዝ ሙሃመድ አስረድተዋል፡፡

ህዝበ ሙስሊሙን በማስተባበር እስከ ግድቡ ፍጻሜ ድረስ ለግድቡ የሚደረገውን ድጋፍ አጠናክረው ለማስቀጠል በትኩረት እንደሚሰሩም ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም