የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የዶናልድ ትራምፕን ንግግር በጽኑ በማውገዝ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት ሊደግፍ ይገባል -- ጄሲ ጃክሰን - ኢዜአ አማርኛ
የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የዶናልድ ትራምፕን ንግግር በጽኑ በማውገዝ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት ሊደግፍ ይገባል -- ጄሲ ጃክሰን
አዲስ አበባ ጥቅምት 20/2013 (ኢዜአ) የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕን ንግግር በጽኑ በማውገዝ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት ሊደግፍ እንደሚገባ አሜሪካዊው የሰብዓዊ መብቶች ተሟጋች ጄሲ ጃክሰን ገለጹ።
‘’የፕሬዚዳንቱ ንግግር ግድየለሽነት የተሞላበት ነው’’ ብለዋል።
የሲቪክ መብቶች ተቋም "ሬንቦው ፑሽ ኮአሊሽን" መስራችና የሰብዓዊ መብት ተሟጋቹ ጄሲ ጃክሰን ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን ዙሪያ ያደረጉትን ንግግር አስመልክቶ መግለጫ አውጥተዋል።
ጄሲ ጃክሰን “ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ግብጽ ግድቡን ልታፈነዳው ትችላለች በማለት ያደረጉት ንግግር ፍጹም ትክክል ያልሆነና ዓለም ሊያወግዘው የሚገባው ነው’’ ብለዋል።
በአሁኑ ሰአት ማንም ቢሆን ፕሬዚዳንቱ በየቀኑ በሚናገሯቸው ሃላፊነት የጎደላቸው ንግግሮችና ተግባራት ብዙም ሊገረም እንደማይገባው ገልጸዋል።
"ትራምፕ በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ጉዳይ ከኢትዮጵያ ይልቅ ሙሉ ድጋፋቸው ለግብጽ እንደሆነ ሁላችንም የምናውቀው ጉዳይ ነው። ይህንንም ለኢትዮጵያ የሚደረገውን እርዳታ በማቋረጥና የዓለም ባንክ በተመሳሳይ ይህን እንዲያደርግ ተጽእኖ በማሳደር አሳይተዋል" ብለዋል ጄሲ ጃክሰን።
ፕሬዚዳንት ትራምፕ ያደረጉት ንግግር ግ ለየትኛውም የዓለም መሪ የማይመጥን እንደሆነም ተናግረዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አቢይ አህመድ ኢትዮጵያ ለየትኛውም አይነት ጠብ አጫሪነትና ሃይል እንደማትበገር መግለጻቸውን ያስታወሱት ጄሲ ጃክሰን፤ “እኔም የማረጋግጠው የኢትዮጵያ ወዳጆች ከእናንተ ጎን መቆማችንን እንደምንቀጥል ነው” ብለዋል።
መሪ አለመግባባቶች ሲፈጠሩ በጦርነት ሳይሆን በሰላማዊ ውይይት እንዲፈቱ ማበረታታት እንዳለበትም አስገንዝበዋል።
‘’የአሜሪካ ኮንግረስ፣ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት፣ የአፍሪካ ህብረት፣ የአውሮፓ ህብረትና ሁሉም ሰላም ወዳድ መሪዎች የፕሬዚዳንቱን ንግግር በጽኑ በማውገዝ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት ሊደግፍ ይገባዋል’’ ነው ያሉት የ79 ዓመቱ የሰብዓዊ መብቶች ተሟጋች።