ቀጥታ፡

ትኩረታችንን ሰላምና ልማት ላይ በማድረግ ያልተነኩ የኢትዮጵያን ሃብቶች ጥቅም ላይ ማዋል አለብን-- ጠ/ሚ ዐቢይ አህመድ

አዲስ አበባ ጥቅምት 20/2013 (ኢዜአ) "ትኩረታችንን ሰላምና ልማት ላይ በማድረግ ለዘመናት ያልተነኩ የኢትዮጵያን ጸጋዎች ጥቅም ላይ ማዋል አለብን" ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ ተናገሩ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህን ያሉት በሶማሌ ክልል የተለያዩ የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክቶችን በይፋ ባስጀመሩበት ወቅት ነው።

በማስጀመሪያ ስነ ስርዓቱ ላይ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ በተጨማሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን፣ የኦሮሚያ ክልል ፕሬዝደንት ሽመልስ አብዲሳ እንዲሁም የሶማሌ ክልል ምክትል ርእሰ መስተዳደር ሙስጠፌ መሃመድ ተገኝተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመጀመሪያ ከጎዴ -ቀላፎ ሎት 1፣ ከጎዴ -ሀርገሌ ሎት1 እንዲሁም ከያአሌ -ደናን ሎት 3 መንገድ ግንባታ ፕሮጀክቶችን ነው በይፋ ያስጀመሩት።

የመንገድ ፕሮጀክቶቹ በድመሩ 277 ነጥብ 6 ኪሎ ሜትር ርዝማኔ ያላቸው ሲሆኑ ለግንባታቸውም 4 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር ተመድቦላቸዋል።

የሶማሌ ክልል ምክትል ፕሬዝዳንት በመርሃ ግበሩ ላይ እንደተናገሩት ከለውጡ በኋላ በሱማሌ ክልል ሰፊ የልማት ስራዎች እየተከናወኑ ይገኛሉ።

የተጀመሩ የመንገድ ስራዎችን ለአብነት አንስተው በተለይ የፌዴራል መንግስት ለክልሉ ለሰጠው ትኩረት ምስጋና አቅርበዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ፤ የሶማሌ ክልል የተፈጥሮ ሃብቶቹን አልምቶ እንዲጠቀም ቀርቶ እራሱን በራሱ እንኳ እንዲያስተዳድር እድል ተነፍጎት የቆየ ክልል መሆኑን አስታውሰዋል።

ይህም ለዘመናት የቆየ ክልሉን ከጦር ካምፕ ግንባታ ጋር ብቻ ከማያያዝ እሳቤ የመነጨ ነበር ብለዋል።

ከለውጡ በኋላ የሱማሌ ተወላጆች ከክልላቸው አልፎ በፌዴራል መንግስት በሃላፊነት በመቀመጥ ኢትዮጵያን ለመለወጥ እየሰሩ ይገኛሉ ነው ያሉት።

ባለፉት ሁለት ዓመታት በክልሉ ከ80 በላይ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች መገንባታቸውን የጠቀሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ በተለይ በመንገድ ዘርፍ ክልሉ ተዘንግቶ የቆየ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

የሱማሌ ክልል ታላላቅ ወንዞች የሚፈሱበት በመሆኑ መንገድን ጨምሮ ሌሎች የመሰረተ ልማት ስራዎችን በማፈጠን ክልሉን የልማት ቀጠና ለማድረግ እንደሚሰራም ነው የተናገሩት።

ወንዞቹን በአግባቡ መጠቀም ከተቻለ እስከ 700 ሺህ ሄክታር መሬት በመስኖ ማልማት እንደሚቻል በመጠቆም።

የመንገድ ፕሮጀክቶቹን ከመጀመር ባለፈ በተቀመጠላቸው ጊዜ እንዲጠናቀቁ ሁሉም የአካባቢው ተወላጆች የበኩላቸውን ሚና እንዲወጡም ጥሪ አቅርበዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሌላው በክልሉ ግንባታውን ያስጀመሩት መንገድ ከጅግጅጋ -ደገሃምዶ- ገለለሽ ያለውን ነው።

መንገዱ 166 ኪሎ ሜትር የሚረዝም ሲሆን ከዚህም ውስጥ ከጅግጅጋ ገለለሽ ያለው 56 ኪ.ሜ በጠቅላይ ሚኒስትሩ  ተመርቆ ለአገልግሎት ክፍት ሆኗል።

ቀሪው ከገለለሽ -ደጋሀመዶ-ሰገግ ያለው 110 ኪ.ሜ መንገድ ግንባታን  በይፋ አስጀምረዋል።

ለግንባታው 1 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር መመደቡን ነው ጠቅላይ ሚኒስትሩ የተናገሩት።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ እንደተናገሩት ለዘመናት ያለፍንበት የግጭት እሳቤ ኢትዮጵያ ያላትን እምቅ ሃብት  እንዳንጠቀምበት አድርጎን ቆይቷል ብለዋል።

ለዚህ ደግሞ ሱማሌ ክልል ያለው ጥቅም ላይ ያልዋሉ  የማዕድንና ሌሎች ሀብቶች ተጠቃሾች ናቸው ።

በመሆኑም ከግጭት ይልቅ ትኩረታችንን ሰላምና ልማት ላይ በማድረግ ለዘመናት ያልተነኩ የኢትዮጵያ ጸጋዎችን ጥቅም ላይ ማዋል አለብን ሲሉም ነው ጥሪ ያቀረቡት።

በሱማሌ ክልል ግንባታቸው ከተጀመሩ መንገዶች መካከል ከጅግጅጋ -ደጋሃምዶ- ገለለሽ ሀገር በቀል በሆነው ቢአይካ ጀኔራል ቢዝነስ የሚገነባ ይሆናል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም