ቀጥታ፡

የድሬዳዋ ኢንዱሰትሪ ፓርክ ለጎረቤት ሀገር ቅርብ መሆኑ ጠቀሜታው የጎላ ነው- ጠቅላይ ሚንስትሩ

ድሬዳዋ፣ ጥቅምት 19/2013(ኢዜአ) በሀገሪቱ ከተገነቡት የኢንዱስትሪ ፓርኮች የድሬዳዋ ለጎረቤት ሀገር ጅቡቲ ቅርብ መሆኑ ጠቀሜታውን የጎላ እንደሚያደርገው ጠቅላይ ሚንስትር ዶክተር አበይ አህመድ አስታወቁ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በ150 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር የተገነባውን የድሬዳዋ የኢንዱስትሪ ፓርክ ማምሻውን በይፋ መርቀው ስራ አስጀምረዋል።


ዶክተር አብይ አህመድ በዚህ ወቅት እንደተናገሩት፤ በሀገሪቱ ከተገነቡት የኢንዱስትሪ ፓርኮች የድሬዳዋ በትክክለኛው ቦታ የተገነባ ነው።

ድሬዳዋና የምስራቁ አካባቢዎች ለኢንዱስትሪው ግብአት የሚሆኑ የተፈጥሮ ሀብትና አስቀድሞ ክህሎትን የታጠቀ የሰው ኃይል በብዛት መገኘታቸው የፓርኩን ተፈላጊነት ያጎላዋል ብለዋል።


ከጎረቤት ጅቡቲ በቅርብ ርቀት መገኘት ብቻ ሳይሆን ከጅቡቲ ጋር በባቡር ፣በአየርና በኮንክሪት አስፓልት መንገድ መገናኘት የሚችለው የዚህ ፓርክ ጠቀሜታ ከፍ እንደሚያደርገው አስታውቀዋል ።


እንደ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገለጻ በፓርኩ ወስጥ ለመኖሪያ የሚያገለግሉ ህንጻዎች ፣ለባለሀብቶች ሁሉንም አገልግሎቶች በአንድ ማዕከል መስጠት የሚያስችሉ ተቋማት መዘጋጀታቸው የፓርኩን ተፈላጊነት ይጨምራል።


የሀገሪቱን እና የድሬዳዋ ሁለንተናዊ የብልፅግና ጉዞ ስኬታማ እንዲሆን፣መሰል ፓርኮች እንዲስፋፉ እና ድሬዳዋ የልማት ፤ እንደስሟ የፍቅር ስፍራ እንድትሆን በመደመር እሳቤ ሁሉም የተጣለበትን ኃላፊነት እንዲወጣም አሳስበዋል ።


የድሬዳዋ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አህመድ መሐመድ የፓርኩ ተመርቆ አገልግሎት መጀመር ድሬዳዋን የምስራቅ የኢንዱስትሪ ከተማ የማድረግ ራዕይ ለማሳካት እና ስራ አጥነትን ትርጉም ባለው መንገድ ለመቀነስ ያስችላል ብለዋል።

የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ሳንዶካን ደበበ በበኩላቸው የኢንደስትሪ ፓርኩ ድሬዳዋን ወደ ቀድሞ የኢንዱስትሪ ኮሪደርነቷ እንደሚመልሳት ተናግረዋል ።


የምስራቅ የሀገሪቱ ክፍልን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ መስተጋብሮች እንደሚያጠናክር ጠቁመው በየደረጃው የሚገኘው ህብረተሰብና አመራር ወደ ፓርኩ ለሚገቡት ባለሀብቶች አስፈላጊውን ድጋፍ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል ።

በምረቃው ሥነ ሥርዓት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን፣የኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት  አቶ ሽመልስ አብዲሳ፣የሶማሌ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳደር አቶ ሙስጠፌ መሐመድ ፣የብልፅግና ፓርቲ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ብናልፍ አንዱአለም ፣የኃይማኖት አባቶች ፣የሀገር ሽማግሌዎችና ሌሎችም አካላት ተገኝተዋል።


ጠቅላይ ሚንስትሩ ዛሬ በሶማሌ ክልል አዳዲስ ግንባታዎችን ካስጀመሩ በኋላ ነው ማምሻውን የድሬዳዋን ኢንዱስትሪ ፓርክ በይፋ የመረቁት ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም