ኢትዮጵያዊያን አንድነታቸውን ይበልጥ በማጠናከር ለሕዳሴው ግድብ ድጋፋቸውን መቀጠል አለባቸው - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያዊያን አንድነታቸውን ይበልጥ በማጠናከር ለሕዳሴው ግድብ ድጋፋቸውን መቀጠል አለባቸው
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 19/2013 (ኢዜአ) ኢትዮጵያዊያን አንድነታችንን ይበልጥ በማጠናከር የሕዳሴው ግድብ ተጠናቆ ኃይል ማመንጨት እስኪጀምር ድጋፋችንን መቀጠል አለብን ሲሉ የእስልምና እምነት ተከታይ አባቶች ተናገሩ።
አባቶቹ የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ የሕዳሴውን ግድብ አስመልክተው የሰጡት አስተያየት ተቀባይነት የለውም ብለዋል።
ኢዜአ 1 ሺህ 495ኛው የነብዩ መሐመድ የልደት በዓል /መውሊድ/ ዛሬ በታላቁ አንዋር መስጊድ ሲከበር ያነጋገራቸው እነዚህ አባቶች ፕሬዚዳንቱ ስለ ግድቡ የሰጡት አስተያየት ኢትዮጵያዊያንን ካለማወቅ የሰነዘሩት እንደሆነ ነው የተናገሩት።
የሃይማኖት አባቶች እንዳሉት የፕሬዚዳንቱ ንግግር ከአንድ የአገር መሪ የማይጠበቅ ነው፡፡
ኢትዮጵያዊያን በአገራቸውና በአንድነታቸው ድርድር እንደማያውቁም ነው የገለፁት።
ቀደምት ኢትዮጵያዊያን መስዋዕት በመሆንና ጠላትን በማዋረድ የአገራቸውን ሉዓላዊነት ማስጠበቃቸውንና የአሁኑ ትውልድም ይህን ታሪክ ለመድገም ወደ ኋላ የማይል መሆኑን ጠቁመዋል።
የፕሬዚዳንት ትራምፕ አስተያየት ስለ ግድቡንም ሆነ ስለ ኢትዮጵያ በቂ መረጃ እንደሌላቸው የሚያሳይ በመሆኑ ኢትዮጵያዊያን ጆሮ መስጠት የለባቸውም ነው ያሉት።
ኢትዮጵያዊያን አንድነታችንን የበለጠ ማጠናከርና፣ ግድቡ ተጠናቆ ኃይል ማመንጨት እስኪጀምር ድረስ የምናደርገውን ድጋፍ አጠናክረን መቀጠል አለብን ሲሉም ተናግረዋል።
በዓሉ የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ቀዳሚ ሙፍቲ ሀጂ ዑመር እድሪስ፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ እና የእምነቱ ተከታዮች በተገኙበት ተከብሯል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ገዱ አንዳርጋቸው የዶናልድ ትራምፕ አስተያየት 'አሜሪካን ከሚመራና ኃላፊነት ከሚሰማው ፕሬዚዳንት የማይጠበቅ፤ በኢትዮጵያና በግብፅ መካከል ጦርነት ቀስቃሽ እንዲሁም በኢትዮጵያና በአሜሪካ መካከል ያለውን የረጅም ጊዜ አጋርነትና ስትራቴጂካዊ ግንኙነት የሚያንፀባርቅ አይደለም' ማለታቸው ይታወሳል።