ዶናልድ ትራምፕ ኢትዮጵያን አስመልክተው ያስተላለፉት መልዕክት ከፍያለ ችግር የሚያስከትል ነው ... በአፍሪካ የውጭ ጉዳዮች አማካሪ ምክር ቤት - ኢዜአ አማርኛ
ዶናልድ ትራምፕ ኢትዮጵያን አስመልክተው ያስተላለፉት መልዕክት ከፍያለ ችግር የሚያስከትል ነው ... በአፍሪካ የውጭ ጉዳዮች አማካሪ ምክር ቤት

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 19/2013(ኢዜአ) ዶናልድ ትራምፕ ኢትዮጵያን አስመልክተው ያስተላለፉት መልዕከት ከፍያለ ችግር የሚያስከትል መሆኑን በአፍሪካ የውጭ ጉዳዮች አማካሪ ምክር ቤት ገለጸ።
ባለፈው ሳምንት ዶናልድ ትራምፕ በቤተ መንግስታቸው ጋዜጠኞችን በመጋበዝ በእስራኤልና በሱዳን መካከል የነበረው ውጥረት መርገቡንና ሠላማዊ ወዳጅነት ለመመስረት መስማማታቸውን አብስረዋል፡፡
ፕሬዚዳንቱ ሪፖርተሮቹን የጋበዙት የዲፕሎማሲ ድላቸውን በማብሰር ስኬታማነታቸውን ለማሳየት ነበር፡፡
በወቅቱ ፕሬዚዳንቱ ከሁለቱ አገራት መሪዎች ጋር በስልክ ከተነጋገሩ በኋላ ግብፅንና ፕሬዚዳንት አብዱልፈታ አልሲሲን በመወከል የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት የሚጋፋና ከጉዳዩ ጋር ተያያዥነት የሌለው መልዕክት አስተላልፈዋል ነው ያሉት በአፍሪካ የውጭ ጉዳዮች አማካሪ ምክር ቤት ፀሃፊ ሚሼል ጋቪን ፡፡
መንግስታቸው የናይልን ወንዝ በተመለከተ ሶስቱን አገራት ለማደራደር ያደረገው ሙከራ አለመሳካቱ ያበሳጫቸው ዶናልድ ትራምፕ "ግብፅ ግድቡን ታፈነዳዋለች ... ከዚህ ያለፈ ነገርም ልታደርግ ትችላለች ...ግንባታውን ማስቆም የነበረባት ዛሬ ሳይሆን በጣም ቀደም ብላ ነበር" በማለት የዲፕሎማሲ ዕውቀት እጥረታቸውን በአደባባይ ማሳየታቸውም ነው የተገለጸው፡፡
አሁን ላይ የህዳሴ ግድቡ ግንባታ በስኬት ከመቀጠሉ ባለፈ የመጀመሪያ ደረጃ የውሃ ሙሌት መያዙን የዘነጉ የመሰሉት ዶናልድ ትራምፕ ለኢትዮጵያ የሚሰጠውን ሰብዓዊ ድጋፍ በመከልከል ለማስፈራራት ሞክረዋል ነው ያሉት፡፡
በዚህም የኢትዮጵያ መንግስት ከያዘው አቋም በማፈግፈግ ለእሳቸው ጥሪ እጅ የሚሰጥ መስሎ ተሰምቷቸው እንደነበርም ተጠቅሷል፡፡
ስትራቴጂካዊ ጠቀሜታው ከፍ ባለው የአፍሪካ ቀንድ አካባቢ ጦርነት የሚያጭር ሐሳብ መሰንዘር ከእብደት ውጭ ምንም ሊባል አይችልም ተብሏል፡፡
አሜሪካ ኢትዮጵያን በማግባባት ስምምነቱን እንድትቀበል አደርጋለሁ ብላ መነሳቷ ታሪካዊ ስህተት ነው ብለዋል ፀሃፊዋ፡፡
ከዚህ የከፋው ደግሞ ፕሬዚዳንቱ የአገራቸውን ፍላጎት ገደል መክተታቸው ነው፡፡
አሜሪካ ለኢትዮጵያ የምትሰጠው ድጋፍ ከልበ ቀናነት የመነጨ ሳይሆን የሁለቱ አገራት ባለስልጣናት እንደሚያውቁት የተረጋጋችና ስኬታማ የሆነች ኢትዮጵያ ለቀጣናው እጀግ አስፈላጊ በመሆኗ ነው፡፡
የኢትዮጵያ ሰላም መሆንና በስኬት ወደፊት መራመድ በቀጣይ ለሚመሰረተው የአሜሪካ-አፍሪካ የጋራ ግንኙነትና የትብብር ራዕይ መሳካት ወሳኝ ነው፡፡
የፕሬዚዳንቱ በግዴለሽ ንግግራቸው አሜሪካ በአፍሪካ የምትከተለውን የተሳሳተ አካሄድ የሚያሳይ የቅርብ ጊዜ ጥሩ ምሳሌ እንደሆነም ተገልጿል፡፡
የአሜሪካ ከፍተኛ ባለስልጣናት አፍሪካ ከቻይና ጋር የጀመረችውን የንግድ ግንኙነት በተመለከተ የተለያዩ ማስጠንቀቂያዎችን እየሰጡ ቢሆንም፤ ፕሬዚዳንቱ ግን ጉዳዩ አሜሪካን ሊያሳጣ የሚችለውን ዘርፈ ብዙ ጥቅም ችላ በማለት ከአፍሪካ ጋር ያለውን አጋርነትና ታማኝነት ገደል መክተታቸው ነው የተገለጸው፡፡
አፍሪካዊያን ወጣቶች ህይወታቸውን ብሩህ ሊያደርግ የሚችልና ተጠያቂነት ያለው መንግስት እንዲኖራቸው እየወተወቱ ባሉበት በዚህ ወቅት የአሜሪካ መንግስት ይህን መፈጸማቸው በሀገራቸው ላይ የማይፈታ ሸምቀቆ እንዳሰረች ይቆጠራልም ብሏል፡፡
አሁን ያለው የአሜሪካ መንግስት በውጭ ጉዳይ ፖሊሲው የአፍሪካን ጉዳይ ችላ ማለቱ በቀጥታ አሜሪካን የሚጎዳው እንደሆነም ጠቅሷል፡፡
የትራምፕ አስተዳደር አፍሪካ እጇን ለውጭ ኃይሎች በቀላሉ የምትሰጥ አድርጎ መገመቱም ጊዜው ያለፈበት የፖለቲካ እሳቤ እንደሚከተል ማሳያ ተደርጎ ተቆጥሯል፡፡
ፕሬዚዳንት ትራምፕ በድጋሚ የሚመረጡ ከሆነ የያዙት አቋም ይቀየራል ብሎ ማሰብ የዋህነት ነው ብለዋል ጸሐፊዋ፡፡
ነገሩ ተለውጦ ባይደን ቢመረጡም አስተዳደራቸው ትራምፕ ለዓመታት ያደረሱትን ጉዳት ተከትሎ ቀጥተኛ ተጽዕኖ ይገጥመዋል የሚል ስጋት እንዳለውም ጠቅሰዋል፡፡
አሜሪካ የተሻለች አፍሪካን ለማየት የምትፈልግ ከሆነ ፖሊሲዋን ማሻሻል፣ ለሁለቱም የሚጠቅም የመጫወቻ ሜዳ ማመቻቸትና አሳታፊነትን ማጎልበት ይጠበቅባታል፡፡
ነገር ግን ጉዳዩ ለአሜሪካ ከፍ ያለ ፈተና በመሆኑ በአስቿኳይ ትኩረት ተሰጥቶ ሊሰራበት እንደሚገባም ፀሃፊዋ አሳስቧል፡፡
"እንደ አለመታደል ሆኖ ታሪክ እንደሚያሳየን ጉዳዩ አዳጋች ነው፣ አዲስ ተመራጩ ፕሬዚዳንት የአፍሪካ ቡድኑን በአፋጣኝ በማዋቀር ወደ ስራ መግባት አለበት" ይላሉ፡፡
ከሁሉ የሚያስከፋው ደግሞ የትራምፕ መንግስት የአፍሪካ ጉዳዮች ተባባሪ ተጠሪ ቲቦር ናጊ ትራምፕ ቃለ መሃላ ከፈጸሙ በኋላ እስከ ጁላይ 2018 ለአንድ ዓመት ተኩል ቢሮ ሳይሰጣቸው መቆየቱ ነው፡፡
አዲሱ የአሜሪካ መንግስት በፍጥነት በመንቀሳቀስ እምነት የሚጣልባቸውን አባላት በማሰባሰብና ግልጽ ራዕይ በማስቀመጥ ከተለመደው አካሄድ ወጣ ያለና ሂደቱን ከስሩ የሚቀይር አሰራር መዘርጋት ይጠበቅበታል በማለት ፀሃፊዋ ምልከታቸውን አስቀምጠዋል፡፡
አፍሪካ በዓለም ዓቀፍ የፖለቲካ ከባቢ ሁኔታ ውስጥ የማይናቅ ሚና መጫወት የምትችል መሆኗንና አሜሪካ ፍላጎቷን ማሳካት እንድትችል ፖሊሲ አውጪዎቿ በቅድሚያ ትራምፕ ከቆፈሩት ጉድጓድ ፈጥነው መውጣት አለባቸው ሲሉም አሳስቧል፡፡