ቀጥታ፡

በህዳሴ ግድብ ላይ የሚስተዋለውን የውጭ ሃይሎች ጫና እናወግዛለን ... በጋምቤላ ክልል የሚገኙ የፓለቲካ ፓርቲዎች

ጋምቤላ፤ ጥቅምት 19/2013( ኢዜአ)ከድህነት ለመውጣት በሚደረገው ጥረት ጉልህ አስተዋጽኦ በሚኖረው የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ላይ የሚስተዋለውን የውጭ ኃይሎች ተጽዕኖ እንደሚያወግዙ በጋምቤላ ክልል የሚገኙ የፓለቲካ ፓርቲዎች አስታወቁ። 

የአሜሪካው ፕሬዘዳንት በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ያሳዩት አድሏዊነት አግባብነት የሌለው መሆኑንም ፓርቲዎቹ ገልጸዋል።

የፓርቲዎቹ አመራሮች ለኢዜአ እንደገለጹት የአሜሪካው ፕሬዘዳንት ዶናልድ ትራምፕ በቅርቡ ለግብጽ በመወገን በህዳሴው ግድብ ግንባታ ዙሪያ ያስተላለፉት መልክት በእጅጉ የሚያሳዝንና የሚስቆጣ ተግባር ነው።

የክልሉ ብልጽግና ፓርቲ ጽህፍት ቤት ኃላፊ አቶ ላክዳር ላክባክ እንደተናገሩት የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ የተጀመረው ኢትዮጵያዊያን በራሳቸው በመተማመን እንጂ ማንንም በማማከር አይደለም። 

"የግድቡ ግንባታ በማንም ጫናና ማስፈራራት የሚቆም አደለም" ያሉት ኃላፊው፤ በኢትየጵያ የተፈጥሮ ሀብት የመወሰን ስልጣን ያለው የአሜሪካ ወይም የግብጽ መንግስት ሳይሆን የኢትዮጵያ ህዝብና መንግስት ብቻ መሆኑንም ተናግረዋል። 

"የህዳሴው ግድብ የኢትዮጵያዊን ታላቅ ሐውልት በመሆኑ በግድቡ ላይ በሚቃጣ ማንኛውም ትንኮሳ የሚደራደር የለም" ብለዋል።

በፓርቲዎች መካከል የፖለቲካ ልዩነቶች እንዳሉ ሆኖ ሁሉም በሀገር ላይ የሚቃጡ ትንኮሳዎችን ለመመከት በጋራና በአንድነት መስራት እንዳሚገባም ነው አቶ ላከደር የተናገሩት።

የጋምቤላ ህዝቦች ነፃነት ንቅናቄ/ ጋህነን /ሊቀመንበር አቶ ፒተር አማን በበኩላቸው የተጀመረውን የልማት ጉዞና የሀገሪቱን ሉዓላዊነት ለመፈታተን የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ለግብጽ በመወገን ያስተለፉት መልዕክት ከአንድ የሀገር መሪ የማይጠበቅ ነው ብለዋል።

ፕሬዘዳንቱ ፍትሐዊነት በጎደለው አድሏዊ አሰራር ለግብጽ በመወገን ባሳዩት አቋም ምክንያት ኢትዮጵያዊያን ካቀዱት የልማት ጉዞ እንደማይደናቀፉ ነው የገለጹት።

"ኢትዮጵያዊያን ከጥንት ጀምሮ ከውጪ የሚቃጣባቸውን ወረራ በአንድነት በመመከት አሳፍረው መመለስ ያውቁበታል" ያሉት ሊቀመበሩ አሁንም በልማቱም ሆነ እራሳቸውን በመከላከል የተለመደውን ታሪካቸውን ለመፈጸም የሚሳናቸው ነገር እንደሌለ አስረድተዋል።

ሀገር ሰላም ስትሆን ነው የፖለቲካ ስራን ማራመድ የሚቻለው ያሉት አቶ ፒተር፤ አሁን ላይ ሁሉም የፓለቲካ ፓርቲዎች ለህዝብና ለሀገር ጥቅም ቅድሚያ በመስጠት በአንድነት ሊሰሩ እንደሚገባ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም