ቀጥታ፡

የፖለቲካ አመራሩ በሰከነና በበሰለ አስተሳሰብ ሊመራ ይገባል - የሠላም ሚኒስትር ሙፈሪያት ካሚል

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 19/2013 (ኢዜአ) የፖለቲካ አመራሩ በሰከነና በበሰለ አስተሳሰብ በመመራት በሠላም ግንባታ ላይ እንዲሰራ የሠላም ሚኒስትሯ ሙፈሪያት ካሚል አሳሰቡ።

ከሁሉም ክልሎች ከወረዳ እስከ ክልል ያሉ ከ600 በላይ የብልጽግና ፓርቲ የፖለቲካ ዘርፍ ሃላፊዎች የተሳተፉበት የሶስት ቀናት አገራዊ የምክክርና የተሳትፎ መድረክ ተካሂዷል።

በመድረኩ በአስተሳሰብና ስሜት ክህሎት፣ በህግ የበላይነትና በዜጎች ክብር፣ በማህበራዊ ሃብቶችና በአዲሱ የፖሊስ ዶክትሪን ላይ ያተኮሩ ስልጠናዎች ተሰጥተዋል።

የምክክር መድረኩ ትናንት ማምሻውን ሲጠናቀቅ የሠላም ሚኒስትሯ በቪዲዮ ኮንፈረንስ ባስተላለፉት መልዕክት ዕድል አግኝተው ህዝብ እየመሩ ያሉ አመራሮች በሰከነና በበሰለ አስተሳሰብ ሊመሩ እንደሚገባ ተናግረዋል።

የስልጠናው ርዕሰ ጉዳዮች ለቀጣዩ ትውልድ በሚሆኑት የሠላም፣ የዴሞክራሲና የልማት አቅጣጫዎች የምትመራ ኢትዮጵያን ለመገንባት ለታለመው ግብ የሚያግዙ በጥንቃቄ የተመረጡ እንደሆኑም ገልፀዋል።

'ባለፉት ዓመታት የመጣንባቸው መንገዶች አሻጋሪ አይደሉም' ያሉት ሚኒስትሯ፤ በየዕለቱ የሚያጋጥሙንን ችግሮች በጠባብ እይታ ሳይሆን አገራዊ ስዕል በመያዝ መወሰን መቻል ይገባል ብለዋል።

አዳዲስ የለውጥ ሃሳቦችና ንድፎችን የያዙ ዕድሎች መኖራቸውን ጠቁመው፤ ካለፈው ስህተት መታረም ያለባቸውን አርሞ፣ መልካሞችን ደግሞ  አጎልብቶ መራመድ እንደሚገባም አስገንዝበዋል።

የሠላም ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ አህመድ ሰይድም ለስልጠናው አሁናዊ የኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታን ብቻ ሳይሆን ነገን ታሳቢ ያደረጉ ይዘቶች መመረጣቸውን ተናግረዋል።

"እንደ አገር ሠላም ለማምጣት አመራሩ መስከን ያስፈልገዋል" ያሉት ኅላፊው፤ ከህብረተሰቡ ጋር በቀጥታ የሚገናኙና መንግስትና ህዝብን የሚያገናኙ ከወረዳ እስከ ክልል ያሉ አመራሮች ላይ መስራት አስፈላጊ መሆኑን ገልጸዋል።

የሠላም እሴት ግንባታን ከግለሰብ ጀምሮ ወደ አገር ለማሳደግ ኢትዮጵያን እንደ ድርና ማግ ያስተሳሰሩ ማህበራዊ ሃብቶች ላይ መስራት ወሳኝ ጉዳይ በመሆኑ በስልጠናው መካተቱን ተናግረዋል።

ስልጠናው በቀጣይ እስከ ታችኛው መንግስታዊ መዋቅር እንደሚወርድም ጠቁመዋል።

አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ የስልጠናው ተሳታፊዎችም ለአመራርነት የሚያግዛቸውን ግብዓት ማግኘታቸውንና ይህንንም ወደ ተግባር ለመተርጎም እንደሚሰሩ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም