ቀጥታ፡

"ሕብረ ብሔራዊነታችን ድምቀታችንና ውበታችን እንጂ አንድነታችንን የሚንድ ምክንያት አይደለም" - ምክትል ከንቲባ አዳነች አቤቤ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 19/2013 (ኢዜአ) "የኢትዮጵያ ሕብረ ብሔራዊነት ድምቀታችንና ውበታችን እንጂ ፈጽሞ አንድነታችንን የሚንድ ምክንያት አይደለም" ሲሉ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ።

1 ሺህ 495 ኛው የነብዩ መሐመድ የልደት በዓል (መውሊድ) ዛሬ በአንዋር መስጊድ ተከብሯል።

የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ አዳነች አበቤ በዚሁ ወቅት እንደገለጹት ኢትዮጵያ የብዙ እምነትና ማንነት ባለቤት ናት።

"የተለያየ እምነት መኖሩ፣ ከተለያየ ብሔር መገኘታችንና የተለያየ ቋንቋ መናገራችን ድምቀታችን፣ ውበታችንና ልዩነታችን እንጂ ፈጽሞ አንድነታችንን የሚንድና የሚያላላ ምክንያት አይደለም" ሲሉ ተናግረዋል።

"ማንነታችንን ጠብቀን ዛሬ ላይ መድረስ የቻልነውና የአፍሪካ የነጻነት ተምሳሌት መባል የቻልነው በአንድነት ስለኖርን ፣ስለተሳሰብንና አብሮነታችን ክፍተት እንዳይገባበት መከላከል ስለቻልን ነው" ብለዋል።

በአንድነታችንና በአብሮነታችን ለሚመጡብን ፈተናዎች በመዘናጋትና ችላ በማለት ክፍተት መስጠት  አይገባም ሲሉም ነው ያሳሰቡት።

"ለብዙ ሺህ ዓመታት ነጻነቷን ጠብቃ ዛሬ ላይ የደረሰችውን ሉዓላዊት አገር ለመዳፈር በገዛ ንብረታችን በገዛ ሀብታችን መጠቀም እንዳንችል የሚፎክሩ አንዳንድ ማስተዋል የሌላቸው መሪዎችን መስማት ጀምረናል" ብለዋል ምክትል ከንቲባዋ።

በራስ ሀብት መጠቀም እና ሉዓላዊነታችንን ማስከበር ኢትዮጵያዊያን ምንጊዜም የማይዘናጉበትና ወደኋላ የማይሉበት ጉዳይ መሆኑንም አንስተዋል፡፡

ጊዜው ከምንጊዜውም በላይ በአንድነትና በአብሮነት መቆም የሚያስፈልግበት ነው ብለዋል ወይዘሮ አዳነች።

በአዲስ አበባ በሚደረገው የሰላም፣ የልማትና አጠቃላይ እንቅስቃሴ ህዝበ ሙስሊሙ እያደረገ ላለው ድጋፍ ምስጋናቸውን ያቀረቡት ምክትል ከንቲባዋ የሚያደርጉትን ድጋፍ አጠናክረው እንዲቀጥሉም ጥሪ አቅርበዋል።

1 ሺህ 495ኛው የነብዩ መሐመድ የልደት በዓል (መውሊድ) የሰላም፣ የአብሮነትና የመተሳሰብ እንዲሆን ምክትል ከንቲባዋ መልካም ምኞታቸውን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም