ቀጥታ፡

በዓሉን ስናከብር ሠላም አንድነትና እኩልነት ለማምጣት የፈጸሙትን ተግባር በመከተል ሊሆን ይገባል - ቀዳሚ ሙፍቲ ሀጂ ዑመር እድሪስ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 19/2013 (ኢዜአ) የነብዩ መሐመድን ልደት ስናከብር ሠላም አንድነትና እኩልነትን ለማምጣት የፈጸሙትን ተግባር በመከተል ሊሆን ይገባል ሲሉ የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ቀዳሚ ሙፍቲ ሀጂ ዑመር እድሪስ አሳሰቡ።


1 ሺህ 495ኛው የነብዩ መሐመድ የልደት በዓል /መውሊድ/ ዛሬ በታላቁ አንዋር መስጊድ ተከብሯል።

የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ቀዳሚ ሙፍቲ ሀጂ ዑመር እድሪስ በዚሁ ጊዜ  በዓል ማክበር ቀናትን፣ ወርና ዓመትን ማምለክ አይደለም ሲሉ ተናግረዋል።

የነብዩ መሐመድን የልደት በዓል ስናከብር ቀኑን ለማስታወስ ሳይሆን እርሳቸው ወደ ምድር ሲላኩ ወደ ሰው ልጆች ምን ይዘው መጡ የሚለውን ማየት ዋናው ጉዳይ እንደሆነ ገልጸዋል።

ነብዩ ወደዚህ ምድር ሲመጡ ለሙስሊሙና ለሌሎች እምነት ተከታዮች መከፋፈል እንደማይጠቅምና ከጠላት ለመጠበቅ በአንድነት መቆም እንደሚገባ ለማስተማር ነው ብለዋል።

ነብዩ መሐመድ ሠላም አታደፍርሱ፣ በሠላም ኑሩ በማለት ይሄንንም በተግባር በመፈጸም በምድር ላይ ሠላምን መመስረታቸውን አመልክተዋል።

ሰው በቀለም፣ በዘር፣ በሀብትና በድህነት በመለያየት ሊበላለጥ አይገባም ማለታቸውን በመጥቀስ ሁሉም ሰው እኩል መሆኑን በማሳወቅ እኩልነትን ያረጋገጡ ነብይ ናቸው ብለዋል።

ነብዩ መሐመድ በሴቶች ላይ የሚፈጸመውንም በደል አይተው ይህ በፍጹም ሊሆን አይገባም ሴቶች ከወንዶች እኩል መብታቸው ሊጠበቅ ይገባል በማለት ማስተማራቸውን ነው ቀዳሚ ሙፍቲ ያስረዱት።

ነብዩ መሐመድ በብሔርና በጎሳ መከፋፈልን በጥብቅ ያወግዙ እንደነበርና ይህም ኋላቀር አስተሳሰብ መሆኑን መግለጻቸውንም አውስተዋል።

በመሆኑም የነብዩ መሐመድን የልደት በዓል ስናከብር ሠላም አንድነትና እኩልነትን ለማስፈን የፈጸሟቸውን ተግባራት በመከተል ሊሆን ይገባል ሲሉ ተናግረዋል።

ያስተማሯቸውን ትምህርቶችና የፈጸሟቸውን ተግባራት ሕዝበ ሙስሊሙና ሰፊው ሕዝብ ሊተገብረውና ሊሰራበት እንደሚገባም አሳስበዋል።

ነብዩ መሐመድ መልካም ባህሪይ፣ ተግባርና አመራር የነበራቸው የመልካምነት ተምሳሌት መሆናቸውንም ነው ቀዳሚ ሙፍቲ ሀጂ ዑመር እድሪስ የገለጹት።

የመውሊድ በዓል ሲከበር ሕዝበ ሙስሊሙ ለተቸገሩ በማብላት፣ በማጠጣትና በማልበስ በመልካም ተግባራት ሊያሳልፈው እንደሚገባም አሳስበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም