ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ ታሳልፋለች እንጂ አታልፍም -- ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ

አዲስ አበባ  ጥቅምት  18/2013 (ኢዜአ) በሺህ ዘመናት አኩሪ ታሪክ ውስጥ ረኀብ፣ ቸነፈር፣ ድርቅና ጎርፍ የደረሰባት ኢትዮጵያ ታሳልፋለች እንጂ አታልፍም ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ገለጹ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ የነብዩ መሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) 1495ኛው ልደት በዓል አስመልክቶ ባስተላለፉት የ’እንኳን አደረሳችሁ’ መልዕክት ላይ እንደገለጹት፤ ኢትዮጵያ የነብዩ መሐመድን (ሰ.ዐ.ወ) ልደት የሚያከብሩ ሙስሊሞች ከክርስቲያኖች፣ ከነባር እምነት ተከታዮች እና ከሌሎችም ወገኖቻቸው ጋር ሆነው በነጻነት ያቆዩዋት አገር ነች፡፡

‘’ዛሬ ከሙስሊም ወገኖቻችን ጋር ሆነን፣ የነብዩ መሐመድን (ሰ.ዐ.ወ) 1495ኛውን ልደት ስናከብር የኢትዮጵያንም ዳግም መወለድ እናስባለን’’ ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ኢትዮጵያ ሕዝቦቿ በእምነቶቻቸው፣ በእድገታቸውና በነጻነታቸው እንደማይደራደሩ ገልጸዋል።

እምነት ለበርካታ ኢትዮጵያውያን ሕይወት በመሆኑ እምነታቸውን በፍጹም ልብ የሚወዱ መሆናቸውን ገልጸዋል።

‘’ዛሬ፣ ከሙስሊም ወገኖቻችን ጋር ሆነን፣ የነብዩ መሐመድን (ሰ.ዐ.ወ) ልደት ስናከብር፣ አገራችን ኢትዮጵያ፣ የአንበጣ መንጋ፣ ጎርፍ፣ ኮቪድ-19 እና ሌሎችም ፈተናዎች እንደተደቀኑባት እያስታወስን ነው’’ ያሉ ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ “ጉዟችን አልጋ በአልጋ እንዳልሆነ ወትሮም እናውቃለን” ብለዋል፡፡

“በየመንገዳችን ላይ እንቅፋት እንደሚኖር እንረዳለን” በማለት ገልጸው፤ “ሙስሊሞች፣ ክርስቲያኖች እና ሌሎችም፣ እንደተለመደው እጅ ለእጅ ተያይዘን፣ ፈተናዎቻችንን ሁሉ እንደምንሻገራቸው ብቻ ሳይሆን፣ የኢትዮጵያውያን ዕድል በኢትዮጵያውን እጅ እንዳለ በፍጹም እናምናለን” ብለዋል፡፡

“እኛ ኢትዮጵያውያን መውሊድን፣ ዒድን፣ ዒድ አል አድሃን በጋራ እና በፍቅር ለማክበር አዲስ እንዳልሆንነው ሁሉ፣ እንደ ሰሞኑ ያሉ ጊዜያዊ ችግሮችንም፣ በጋራ ለማሸነፍ እና ወደ ፊት ለመራመድ አዲሶች አይደለንም’’ ሲሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

‘’በሺህ ዘመናት አኩሪ ታሪካችን ውስጥ፣ ረኀብም፣ ቸነፈርም፣ ድርቅም፣ ጎርፍም፣ ደርሰውብን፣ ሁሉንም አልፈን ነው እዚህ የደረስነው፡፡ ኢትዮጵያ ታሳልፋለች እንጂ አታልፍም’’ ብለዋል።

ነብዩ መሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) በመካ ሲያስተምሩ፤ የተቀበሏቸው ጥቂት፣ የተቃወሟቸው ብዙ እንደነበሩ አስታውሰው፤ ያመጡትን ለውጥ ለማስቀረት ብዙ ቢደከምም ብዙዎች እየቆዩ እንደተረዷቸውና ከጎናቸው እንደቆሙ ጠቅሰዋል።

‘’የኛም የለውጥ ጉዞ እንዲሁ ነው’’ በማለት የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ‘’በቆየው ኢትዮጵያዊ የመተዛዘን እና የመረዳዳት ባሕል ታላቁን የመውሊድ በዓል፣ ቤታችን ሆነን ስናከብር፣ ቤት የሌላቸው፣ ወይም በጎርፍም ሆነ በሌላ አደጋ ቤቶቻቸውን ያጡ፣ ከሚኖሩበት ተፈናቅለው፣ በየቦታው የተጠለሉ ወገኖቻችንን እናስታውስ’’ ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል።

“ምንም ባይኖረን እንኳ፣ ፍቅር እንስጣቸው፡፡ ፍቅር፣ ከሁሉ ነገር ይበልጣል፡፡ መተሳሰብ እና መደጋገፍ ታላቅ ወንዝ፣ ታላቅ ፈተናን ያሻግራል፡፡ ችግር፣ የጊዜ ጉዳይ ነው።’’ ብለዋል በመልዕክታቸው።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ያስተላለፉት ሙሉ መልእክት እንደሚከተለው ቀርቧል።

 ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የነብዩ መሐመድ(ሰ.ዐ.ወ) 1495ኛው ልደት በዓል በተመለከተ ያስተላለፉት የእንኳን አደረሳችሁ መልእክት፤ ኢትየጵያችን፣ የነብዩ መሐመድን (ሰዐወ) ልደት የሚያከብሩ ሙስሊሞች፣ ከክርስቲያኖች፣ ከነባር እምነት ተከታዮች እና ከሌሎችም ወገኖቻቸው ጋር ሆነው፣ ለዘመናት በነጻነት ያቆዩዋት ሀገር ነች፡፡

ዛሬ ከሙስሊም ወገኖቻችን ጋር ሆነን፣ የነብዩ መሐመድን (ሰዐወ) 1495ኛውን ልደት ስናከብር፣ የኢትዮጵያንም ዳግም መወለድ እናስባለን፡፡ ስለ ሕዝቦቿ ነጻነት እና ብልጽግና እንጨነቃለን፡፡

ኢትዮጵያ፣ የእስልምና፣ የክርስትና፣ እና የሌሎችም ነባር እምነቶች ሀገር በመሆኗ፣ ሕዝቦቿ፣ በእምነቶቻቸው አይደራደሩም፡፡ በእድገታቸው አይደራደሩም፡፡

በነጻነታቸውም ቀልድ አያውቁም፡፡ እምነት፣ ለበርካታ ኢትዮጵያውያን፣ ሕይወት ነው ፡፡ ለዚህ ነው፣ እምነታቸውን በፍጹም ልብ የሚወዱት፤ ለዚህ ነው፣ በእምነታቸው የማይደራደሩት፡፡ ለዚህም ነው፣ ታላቁን የመውሊድ በዓል፣ በእንዲህ ዓይነት ድምቀት የሚያከብሩት፡፡

እንኳን ለ1495ኛው፣ ለታላቁ የመውሊድ በዓል በሰላም አደረሳችሁ! መውሊደል ነቢ፣ ራቢዩላወል በተሰኘው ወር፣ በ12ኛው ቀን፣ በመካ የተወለዱት፣ የእስልምና ሃይማኖት መሥራች እና የአላህን ቁርዐን ለሰው ልጆች ያወጁት፣ የታላቁ የእስልምና ነቢይ የልደት በዓል ነው፣ ዛሬ፡፡

ይህ ታላቅ ቀን፣ በቢልዮኖች በሚቆጠሩ የዓለም ሙስሊሞች፣ በሚልዮኖች በሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች እና በወገኖቻቸው ሁሉ በድምቀት ይከበራል፡፡

በቅድመ ኮቪድ ጊዜ እንደነበረው፣ ሰዎች ከገር ሀገር እየዞሩ፣ ከወዳጅ ዘመዶቻቸው ጋር በብዛት እየተሰባሰቡ ባይሆንም፣ ቀኑ ታላቅ ነው እና ልደቱም የነብዩ መሐመድ (ሰዐወ) ነውና በመስጊዶች፣ በመድረሳዎችና መጅሊሶች በፍቅር እና በታላቅ ስሜት ይከበራል፡፡ የነብዩ ልደት ፣ ሥራ እና ሕይወት፣ ይዘከራል።

ዛሬ፣ ከሙስሊም ወገኖቻችን ጋር ሆነን፣ የነብዩ መሐመድን (ሰዐወ) ልደት ስናከብር፣ ሀገራችን ኢትዮጵያ፣ የአንበጣ መንጋ፣ ጎርፍ፣ ኮቪድ 19 እና ሌሎችም ፈተናዎች እንደተደቀኑባት እያስታወስን ነው፡፡ ጉዟችን አልጋ በአልጋ እንዳልሆነ ወትሮም እናውቃለን፡፡

በየመንገዳችን ላይ እንቅፋት እንደሚኖር እንረዳለን፡፡ ያም ሁሉ ሆኖ፣ ሙስሊሞች፣ ክርስቲያኖች እና ሌሎችም፣ እንደተለመደው እጅ ለእጅ ተያይዘን፣ ፈተናዎቻችንን ሁሉ እንደምንሻገራቸው ብቻ ሳይሆን፣ የኢትዮጵያውያን ዕድል በኢትዮጵያውን እጅ እንዳለ በፍጹም እናምናለን፡፡

ታላቁን የመውሊድ በዓል ስናከብር፣ ምንጊዜም ልብ ልንለው የሚገባ ሌላም ቁም ነገር አለ፡፡

እኛ ኢትዮጵያውያን መውሊድን፣ ዒድን፣ ዒድ አል አድሃን በጋራ እና በፍቅር ለማክበር አዲስ እንዳልሆንነው ሁሉ፣ እንደ ሰሞኑ ያሉ ጊዜያዊ ችግሮችንም፣ በጋራ ለማሸነፍ እና ወደ ፊት ለመራመድ አዲሶች አይደለንም፡፡

በሺህ ዘመናት አኩሪ ታሪካችን ውስጥ፣ ረኀብም፣ ቸነፈርም፣ ድርቅም፣ ጎርፍም፣ ደርሰውብን፣ ሁሉንም አልፈን ነው እዚህ የደረስነው፡፡ ኢትዮጵያ ታሳልፋለች እንጂ አታልፍም። ነብዩ መሐመድ (ሰዐወ) በመካ ተወልደው ሲያስተምሩ፤ የተቀበሏቸው ጥቂት፣ የተቃወሟቸው ብዙ ነበሩ። ብዙዎች እየቆዩ ነው የተረዷቸው።

ያመጡትን ለውጥ ለማስቀረት ብዙ ተደክሟል። በጽናት፣ በተጋድሎና በጊዜ ውስጥ ግን ብዙዎች ከጎናቸው ቆመዋል።

የኛም የለውጥ ጉዞ እንዲሁ ነው። በቆየው ኢትዮጵያዊ የመተዛዘን እና የመረዳዳት ባሕል ታላቁን የመውሊድ በዓል፣ ቤታችን ሆነን ስናከብር፣ ቤት የሌላቸው፣ ወይም በጎርፍም ሆነ በሌላ አደጋ ቤቶቻቸውን ያጡ፣ ከሚኖሩበት ተፈናቅለው፣ በየቦታው የተጠለሉ ወገኖቻችንን እናስታውስ፡፡

ስንበላ ስንጠጣ፣ የሚበሉት የሚጠጡት የሌላቸው፣ ያዘኑ፣ የተቸገሩ፣ ብዙዎች እንዳሉም አንርሳ፡፡ በልዩ ልዩ ምክንያት እንዲህ ለጊዜው የተቸገሩ ወንድም እኅቶቻችን እና ልጆቻችን፣ በአሉን አብረውን እንዲያከብሩ፣ ያለንን እናካፍላቸው፡፡ የምንችለውን እናድርግላቸው፡፡ ምንም ባይኖረን እንኳ፣ ፍቅር እንስጣቸው፡፡ ፍቅር፣ ከሁሉ ነገር ይበልጣል፡፡

መተሳሰብ እና መደጋገፍ ታላቅ ወንዝ፣ ታላቅ ፈተናን ያሻግራል፡፡ ችግር፣ የጊዜ ጉዳይ ነው። በዓሉ ነገ ስለሚጠብቀን መልካም ጊዜ እያሰብን፣ በፍቅር እና በደስታ የምናከብረው በዓል ይሁንልን፡፡ ሁላችንም ተሳስበን፣ ከበሽታ ርቀን፣ ጤንነታችንን ጠብቀን፣ ሌሎችም እንዳይታመሙ አግዘን፣ የምናከብረው፣ የፍቅር በአል ይሁን፡፡

በድጋሚ፣ ሁላችንንም፣ እንኳን፣ ለመውሊድ በዓል አደረሰን! እንኳን አደረሳችሁ! ኢትዮጵያ በልጆቿ ጥረት ታፍራና ተከብራ ለዘላለም ትኑር!! ፈጣሪ ኢትዮጵያና ሕዝቦቿን ይባርክ!

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም