ቀጥታ፡

ለኢትዮጵያ ሉአላዊነትና ሰላም ከመንግስትና ከህዝብ ጋር እንሰራለን- የቀድሞ የኢትዮጵያ ሠራዊት አባላት

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 18/2013 ( ኢዜአ) የኢትዮጵያን ዕድገት፣ ሰላምና ሉአላዊነት ለማስቀጠል ከመንግስትና ከህዝብ ጋር እንደሚቆሙ የቀድሞ የኢትዮጵያ ሠራዊት አባላት ተናገሩ።

ሰሞኑን በሕዳሴው ግድብ ላይ የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ የተሰጠው አስተያየት እንዳሳዘናቸው የገለጹት የቀድሞ ሠራዊት አባላት ግድቡን በጉልበት፣ በገንዘብና በሙያቸው ለመደገፍ ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ በራሷ አቅም የሕዳሴውን ግድብ እየገነባች መሆኑ የከፍታዋን ጉዞ ያፋጥነዋል የሚል እምነት እንዳላቸው ገልጸው፤ የኢትዮጵያን የልማት ጉዞ ለማፋጠን በሚከናወኑ ተግባራት ከመንግስትና ከህዝብ ጎን እንደሚቆሙ አረጋግጠዋል።

የቀድሞ የኢትዮጵያ ሠራዊት የድጋፍና የልማት ማህበር ፕሬዚዳንት ሃምሳ አለቃ ብርሃኑ አማረ ለሕዳሴው ግድብ በጉልበት፣ በገንዘብና በሙያቸው ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል።

የአሜሪካው ፕሬዚዳንት የሕዳሴውን ግድብ አስመልክተው በቅርቡ የሰጡት አስተያየት አግባብነት እንደሌለው ተናግረው፤  "ይህም ኢትዮጵያንና ህዝቦቿን በአግባቡ ካለማወቅ የተሰጠ ነው" ብለዋል።  

የነጻነት ተምሳሌት የሆነችውን ኢትዮጵያ እድገቷን፣ ሰላሟንና ሉአላዊነቷን ጠብቆ ለማቆየት የቀድሞ የኢትዮጵያ ሠራዊት አባላት ከመንግስትና ከህዝቡ ጋር ተባብረው ለመስራት ዝግጁ መሆናቸውን አመልክተዋል።

ሌላው የማህበሩ አባል መቶ አለቃ ታሪኩ በቀለ በበኩላቸው ''በየዘመኑ መንግስታት ቢቀያየሩም የአገር ሠራዊት ሁሌም ለአገርና ለህዝብ የሚከፈልን ዋጋ ሲከፍል የቆየና በቀጣይም ለመክፈል የተዘጋጀ ነው'' ሲሉ ገልጸዋል።

የቀድሞ የኢትዮጵያ ሠራዊት የድጋፍና የልማት ማህበር አንድ ሚሊዮን አባላት እንዳሉት ጠቁመው፤ መንግስት አባላቱ እንዲያግዙ በሚፈልገው መስክ ሁሉ ለማገልገል ፈቃደኛ መሆናቸውን አረጋግጠዋል።

''ኢትዮጵያ በታሪኳ የምትታወቀው በሉአላዊነቷና በአንድነቷ ላይ የመጣን ጠላት መክታና አስተምራ ለጥቁር ህዝቦች ሁሉ ተምሳሌት በመሆን ነው" ያሉት መቶ አለቃ ታሪኩ፤ ዛሬም ኢትዮጵያ ይህን ታሪክ የሚደግሙ ልጆች እንዳሏት ተናግረዋል።

የኢትዮጵያን እድገትና አንድነት በማይፈልጉ አካላት በተለያዩ ጊዜያት በውስጥና በውጭ የሚቃጡ እኩይ ተግባራትን በመመከት የአገሪቷን ሉአላዊነት ለማስጠበቅና ዕድገቷን ለማስቀጠል በሚከናወኑ ተግባራት የድርሻቸውን እንደሚወጡም አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም