በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የመማር ማስተማር ሂደቱን ሰላማዊ ለማድረግ እየተሰራ ነው

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 17/2013 ( ኢዜአ) በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የመማር ማስተማር ሂደቱን ሰላማዊ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑ ተገለጸ።

በተቋማቱ ፀጥታን ለሚያስጠብቁ የፌዴራል ፖሊስ አባላት አመራሮች የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥልጠና እየተሰጠ ነው።

ስልጠናው የተማሪዎች እና የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ባህሪያት ምን እንደሆኑ ግንዛቤ ለማስጨበጥ ያለመ ነው ተብሏል።

በሥልጠናው የሰላም ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ፍሬዓለም ሽባባው፣ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ሳሙኤል ክፍሌ እና የፌዴራል ፖሊስ የወንጀል መከላከል ዘርፍ ምክትል ኮሚሽነር ጄነራል መላኩ ፋንታ ተገኝተዋል።

በስልጠናው መክፈቻ ላይ ንግግር ያደረጉት የሰላም ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ፍሬዓለም ሽባባው ስልጠናው እየተሰጠ ያለው በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚሰጠውን የመማር ማስተማር ሂደት ሰላማዊ ለማድረግ ታስቦ መሆኑን ተናግረዋል።

የፀጥታ አካላት በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በሚሰማሩበት ወቅት የተማሪዎችን እና የተቋማቱን ባህሪ ከወዲሁ ተረድተው የፀጥታ ተግባራቸውን በመርህ ላይ በመመስረት እንዲያከናውኑ ለማድረግ ጭምር መሆኑንም ነው የገለጹት።

"የፀጥታ ኃይሎችም በትምህርት ተቋማቱ በሚሰማሩበት ወቅት ለተማሪዎች ምክር ሰጪ፣ ሰላማቸውን የሚጠብቁና እና ቦታዎችን አመላካች መሆን አለባችሁ" ብለዋል።

ከፍተኛ ትምህርት ተቋማቱም የኮቪድ-19 ወረርሽኝን ለመከላከል በጤና ሚኒስቴር የወጡ መመሪያዎችን በማስተግበር፣ የመማር ማስተማር ሂደቱን ሰላማዊ ማድረግ እንዳለባቸውም ሚኒስትር ዴኤታዋ ተናግረዋል።

"ወይዘሮ ፍሬዓለም የጸጥታ አካላት ለተማሪዎች አስፈላጊውን ጥበቃ በማድረግ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ምንም አይነት የጸጥታ ስጋት እንዳይገጥም ማድረግ አለባችሁ" ሲሉም አሳስበዋል።

የፌዴራል ፖሊስ የወንጀል መከላከል ዘርፍ ምክትል ኮሚሽነር ጄነራል መላኩ ፋንታ ለጸጥታ አካላት ስልጠና እየተሰጠ ያለው በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ያለምንም የጸጥታ ችግር ሰላማዊ የመማር ማስተማር ሂደት እንዲኖር ለማድረግ መሆኑን ገልጸዋል።

"ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ከማንኛውም የፖለቲካ አስተሳሰብ ነጻ ሆነው የትምህርት፣ የምርምርና የጥናት ተቋማት እንዲሆኑ ለማድረግ ነው" ሲሉም ምክትል ኮሚሽነሩ ተናግረዋል።

የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ሳሙኤል ክፍሌ በበኩላቸው ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በራሳቸው የጥበቃ አካላት መጠበቅ እንዳለባቸው ጠቁመዋል።

ይሁንና ከ2013 ዓመት ጀምሮ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የውስጥ የጸጥታ አቅም እስኪጠናከር ድረስ ሁሉም የመንግስት ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት በተጨማሪነት በፌዴራል ፖሊስ አባላት እንደሚጠበቁ ተናግረዋል።

የትምህርት ተቋማቱ በፌዴራል ፖሊስ እንዲጠበቁ የሚደረገው ባለፉት ዓመታት በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የተፈጠሩ ችግሮች ዳግም እንዳይከሰቱ ወላጆች በእምነት ልጆቻቸውን እንዲልኩና ተማሪዎች ደህንነት ተሰምቷቸው ትምህርታቸውን እንዲከታተሉ ለማድረግ መሆኑን ዶክተር ሳሙኤል አስረድተዋል።

ሥልጠናው በሰላም ሚኒስቴር እና በሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ትብብር የተዘጋጀ ሲሆን ለተከታታይ ሁለት ቀናት እንደሚካሄድ ታውቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም