ቀጥታ፡

ለታላቁ የኢትዮጰያ ህዳሴ ግድብ ድጋፋቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ በዴዶ ወረዳ ነዋሪዎች ገለጹ

ጅማ ጥቅምት 17/2013 ( ኢዜአ) ለታላቁ ህዳሴ ግድብ የሚያደርጉትን ድጋፍ አጠናክረው እንደሚቀጥሉ በጅማ ዞን ዴዶ ወረዳ ነዋሪዎች ገለጹ፡፡

ነዋሪዎቹ ጥቅምት 15/2013 ለግድቡ ግንባታ ድጋፍ እንዲውል 42  የደለቡ ሰንጋዎችን እና አንድ በግ ለግሰዋል፡፡

ድጋፍ ካደረጉት መካከል አቶ አብዱልከሪም አባራያ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በታላቁ ህዳሴ ግድብ ዙሪያ የሚደረገው የወጭ ጣልቃ ገብነት እንዳሳዘናቸው ገልፀው፣ ለግድቡ ስራ መጠናቀቅ የሚያደርጉትን ድጋፍ አጠናክረው ለመቀጠል መወሰናቸውን ገልጸዋል።

አቶ አማን አባሳንቢ በበኩላቸው የወረዳውን ነዋሪዎች አስተባብረው  ከ100 ብር አንስቶ እስከ 2 ሺህ 5 መቶ ብር በማዋጣት የደለቡ ሰንጋዎችን  በመግዛት ለታላቁ ህዳሴ ግደብ አስተዋጽኦ ማድረጋቸው ተናግረዋል።

የግድቡ የመጀመሪያው ዙር የውሃ ሙሌት በስኬት መጠናቀቅ በፈጠረባቸው መነሳሳት አስተዋጽኦ ማበርከታቸውን አመልክተዋል።

ኢትዮጵያ የህዳሴውን ግድብ በቁርጠኝት ለማጠናቀቅ መቃረቧ ያላስደሰታቸው የውጭ ሀገራት በውስጥ አለመረጋጋት እንዲፈጠር በስፋት እየሰሩ መሆኑን መገንዘባቸውን አስረድተዋል፡፡

ይህ ድርጊታቸውም የኢትዮጵያን ታሪክ በተለይም ለቀኝ ገዥዎች ፍላጎት የማንበረከክ ህዝቦች መሆናችንን ካለመረዳት የመጣ ነው ብለዋል።

"ግብጽ ከቅኝ ተገዥነት መንፈስ ያልተላቀቀች ሀገር ናት፣ አንዳንዴም የቅኝ ገዢዎች ያወጡት ህግ ተገባራዊ እንዲሆን ትፈለጋለች፣ አልሳካ ሲላት ደግሞ ወደ አረብ ሀገራት በመጠጋት በኢትዮጵያ ጥቅም ለመደራደር ትሞክራለች" ብለዋል።

የነዋሪዎቹ ያበረከቱትን ድጋፍ የተረከቡት የዴዶ ወረዳ አስተዳደሪ አቶ አህመድ ቢያ  የወረዳው ህዝብ ለህዳሴ ግድብ በዚህ ወሳኝ ወቅት ያደረጉት ድጋፍ የሚበረታታ ነው ብለዋል።

የወረዳው ነዋሪዎች በሀገሪቱ ላይ የሚደረገው ኢ-ፍትሃዊ ጣልቃ ግብነት በመረዳትና በተግባር ምላሽ ለመስጠት ያደረጉት  መነሳሳት በሌሎች የኢትዮጵያ አካባቢዎች መቀጠል እንዳለበትም አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም