ቀጥታ፡

መርሃ ግብሩ የህብረተሰቡን የቁጠባ ባህልና የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ለማሳደግ ጠቀሜታው የጎላ መሆኑ ተገለጸ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 17/2013 ( ኢዜአ) የይቆጥቡ ይሸለሙ መርሃግብር የህብረተሰቡን የቁጠባ ባህል በማዳበር የኢኮኖሚ ተጠቃሚነቱን ለማሳደግ ጠቀሜታው የጎላ መሆኑ ተገለጸ።

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ 9ኛው ዙር የይቆጥቡ ይሸለሙ የዕጣ አወጣጥ መርሃ ግብር ዛሬ በብሔራዊ ሎቶሪ አስተዳደር ቅጥር ግቢ ተከናውኗል።

በዕጣ አወጣጥ መርሃ ግብሩ ላይ የተገኙት የባንኩ ፕሬዚዳንት አቶ አቤ ሳኖ የይቆጥቡ ይሸለሙ መርሃ ግብር ከ2 ሚሊዮን የማይበልጡ ሰዎች በተሳተፉበት በ2010 ዓ.ም መጀመሩን አስታውሰዋል።

በወቅቱ ቁጠባው ከ56 ቢሊዮን ብር የማይበልጥ እንደነበር አስታውሰው በአሁኑ ወቅት የተሳታፊዎች ቁጥር ከ26 ሚሊዮን በላይ መሆኑንና ቁጠባውም ከ655 ቢሊዮን ብር በላይ መድረሱን ተናግረዋል።

የይቆጥቡ ይሸለሙ መርሃ ግብር የህብረተሰቡን የቁጠባ ባህል በማዳበር የኢኮኖሚ ተጠቃሚነቱን በማረጋገጥ በኩል ጠቀሜታው የጎላ መሆኑንም ፕሬዚዳንቱ ገልጸዋል።

"የይቆጥቡ ይሸለሙ መርሃ ግበር የባንክ አገልግሎትን ከማስፋት አንጻርም ጉልህ ድርሻ አለው" ነው ያሉት።

እንደ አቶ አቤ ገለጻ 9ኛው ዙር የይቆጥቡ ይሸለሙ መርሃ ግብር 50 ከፍተኛ ሽልማቶችን የያዘ ሲሆን ከእነዚህ ውስጥ ሁለት ደረጃቸውን የጠበቁ  አፓርትመንት ቤቶችና ሦስት የጭነት ተሽከርካሪዎች ይገኙበታል።

ከእዚህ በተጨማሪ 15 ዘመናዊ አውቶሞቢሎችና 30 ባለ ሦስት ዕግር ተሽከርካሪዎች በዕጣው መካተታቸውም ተመልክቷል።

ባንኩ ለሽልማቱ ከ40 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ ማድረጉን ፕሬዚዳንቱ ተናግረዋል።

በንግድ ባንክ የቁጠባ ሒሳብ ከፍተው ከ500 ብር ጀምሮ የቆጠቡ ሰዎች የእጣው ተሳታፊ እንደሚሆኑ የተናገሩት ፕሬዚዳንቱ፣ በቀጣይም ሁሉም ዜጋ የቁጠባ ባህሉን በማዳበር የዚህ ዕድል ተጠቃሚ እንዲሆን ጥሪ አቅርበዋል።

የዕጣ አወጣጥ ስርአቱ ዛሬ በብሔራዊ ሎተሪ አስተዳደር ቅጥር ግቢ ተከናውኗል።

"በቀጣይም በባንኩ የውጭ ምንዛሬ ለሚያካሂዱ ደንበኞቹም የሽልማት መርሃ ግብር ለማዘጋጀት እየሰራ ነው" ብለዋል።

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ተሞክሮን በመውሰድ ሌሎች ባንኮችም መሰል የሽልማት አሰራሮችን በመተግበር የህብረተሰቡን የቁጠባ ባህል እያዳበሩ መሆኑንም አቶ አቤ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም