ቀጥታ፡

'አንዱ አንዱን መግደል የእንስሳት እንጂ የሰው ልጆች ባህሪ አይደለም"'- ቀዳሚ ሙፍቲ ሃጂ ዑመር እንድሪስ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 17/2013 ( ኢዜአ) ''አንዱ አንዱን መግደል የእንስሳት እንጂ የሰው ልጆች ባህሪ ባለመሆኑ ሊቆም ይገባል'' ሲሉ የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ቀዳሚ ሙፍቲ ሃጂ ዑመር እንድሪስ ተናገሩ። 

ቀዳሚ ሙፍቲ ሃጂ ዑመር እንድሪስ  የፊታችን ሀሙስ የሚከበረውን 1 ሺህ 495ኛው የነብዩ ሙሀመድ መውሊድ በዓል በማስመልከት መልዕክት አስተላልፈዋል።     

ፕሬዝዳንቱ በመልዕክታቸው "ነብዩ ሙሀመድ በምድር ቆይታቸው በጎ ነገሮችን ሰርተው አልፈዋል፤ በመወለዳቸው ምክንያት የሰው ልጅን መከራን አስቀርተዋል''ብለዋል።    

ነብዩ ሙሀመድ "የሰውን ልጅ ከጥፋት መልሰውታል በዚህም ይደርስበት የነበረው ርሃብና ድርቅም ተነስቶለታል'' ያሉት ፕሬዝዳንቱ አሁንም ሁሉም የእምነቱ ተከታይ የእርሳቸውን መልካም ስራዎች በተግባር ማሳየት አለበት ብለዋል።   

''ማንም ሰው በህይወት እስካለ ድረስ የነብያችንን አደራ፣ አመራርና መልካም ጠባይ ሊከተል ይገባል'' ሲሉም አሳስበዋል።    

ቀዳሚ ሙፍቲ ሃጂ ዑመር እንድሪስ በመግለጫቸው በጉራ ፈርዳ ወረዳ በንጹሃን ዜጎች ላይ የደረሰውን ጥቃትም በጽኑ አውግዘዋል።

"ኢትዮጵያዊያን መተዛዘን፣ አብሮ መብላት፣ መረዳዳት እንጂ መገዳደል፣ ደም መቃባት ባህላችን አይደለም'' ያሉት ፕሬዝዳንቱ "ወደ አውሬነት ልንመለስ አይገባም" ብለዋል።   

"አንዱ አንዱን መግደል ማሰቃየት የአውሬነት እንጂ የሰው ባህሪ ባለመሆኑ ሊቆም ይገባዋልም ነው ያሉት።  

"ሁላችንም ሰላማችንን መጠበቅ በመከባበርና መተዛዘን አንድነትን በማጠናከር የድርሻችንን እንወጣ " ሲሉም ጥሪ አቅርበዋል።  

የአንበጣ መንጋ እያደረሰ ያለውን ጉዳት ለመከላከልም ከልባችን ወደ ፈጣሪያችን በመመለስ ዱዓ እናድርግ ብለዋል።

ከበደል የንጹሃንን ደም ከማፍሰስና ከሀጥያት እስካልተቆጠብን ድረስ ወደፊት ከአንበጣም ሌላ መከራ ሊመጣ ይችላልና የእምነቱን አስተምህሮ በመከተል ከሙስና፣ ከሌብነትና በደል ራስን ማራቅ ያስፈልጋል ብለዋል።  

በአባይ ውሃ ላይ ለመጠቀም የተጀመረውን የህዳሴ ግድብ ግንባታ በተመለከተ የአሜሪካው ፕሬዝዳንት የሰጡት አስተያየትም የሚወገዝና ተቀባይነት የሌለው መሆኑን አንስተዋል።

ፕሬዝዳንቱ በመግለጫቸው ለሰላት ወደ መስጊድ የሚገቡ ምዕመናን ባለመጨባበጥና ርቀትን በመጠበቅ ራሳቸውንና ቤተሰባቸውን ከኮሮና ቫይረስ እንዲጠብቁም አሳስበዋል።

የፊታችን ሀሙስ የሚከበረው የመውሊድ በዓል መልካም እንዲሆን ለመላው የእምነቱ ተከታዮች መልእክታቸውን አስተላልፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም