ጨው በማምረት ሥራ የተሰማሩ ባለሃብቶች እሴት ያለተጨመረበት ጥሬ ጨው ማምረት አይችሉም -- የማዕድንና ነዳጅ ሚኒስቴር - ኢዜአ አማርኛ
ጨው በማምረት ሥራ የተሰማሩ ባለሃብቶች እሴት ያለተጨመረበት ጥሬ ጨው ማምረት አይችሉም -- የማዕድንና ነዳጅ ሚኒስቴር
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 16/2013 ( ኢዜአ) በአፋር ክልል ጨው በማምረት ሥራ የሚሰማሩ ባለሃብቶች እሴት ያልተጨመረበት ጥሬ ጨው ማምረት እንደማይችሉ የማዕድንና ነዳጅ ሚኒስቴር ገለጸ።
የማዕድንና ነዳጅ ሚኒስትር ኢንጂነር ታከለ ኡማና የአፋር ክልል ርዕሰ መስተዳደር አቶ አወል አርባ በአፍዴራ የጨው ማምረቻ ተገኝተው ጉብኝት አድርገዋል።
በኢትዮጵያዊያንና በቱርክ ባለሃብቶች ትብብር የተገነባውን ቲ.ቲ.አር. የአዮዳይዝድ ጨው መምረቻ ፋብሪካ፣ በቻይናውያን ባለሃብቶች የሚገነባውን ታናርሙ የተባለ የብሮሚን ማዕድን ማምረቻ ፋብሪካ እንዲሁም ወጣቶች ተደራጅተው የሚያመርቱትን ጥሬ ጨው ጎብኝተዋል።
የማዕድንና ነዳጅ ሚኒስትሩ ኢንጂነር ታከለ ዑማ በእዚህ ወቅት እንዳሉት በአፋር ክልል ያለው የማዕድን ሀብት ኢትዮጵያን መቀየር የሚችል ነው
"በኢትዮጵያ አፍዴራ ጨው እያለ ምርቱን አዮዲን ቀላቅሎ ለገበያ የሚያቀርብ ድርጅት ባለመኖሩ ዛሬም በብዙ ሰዎች ላይ የአዮዲን እጥረት ይስተዋላል" ብለዋል።
በመሆኑም ከየትኛውም አካባቢ መጥተው በአፍዴራ ጨው ለማምረት የሚሰማሩ ባለሃብቶች እሴት በሚጨምር እንጂ ጥሬ ጨው በማምረት መሳተፍ እንደሌለባቸው ተናግረዋል።
"በአካባቢው ያለው ማህበረሰብ የሐይቁን ተፈጥሯዊ ውሃ ተጠቅሞ ማምረት በሚችለው ሥራ ላይ ሌላ ባለሃብት የሚሰራ ከሆነ ትክክል አይደለም" ብለዋል።
"በሐይቆቹ ያለውን የተፈጥሮ ሃብት በሚገባ ለመጠቀም የአካባቢው ወጣቶች ብቻ መሳተፍ ይገባቸዋል" ብለዋል ሚኒስትሩ ኢንጂነር ታከለ ኡማ።
ከዚህ አልፎ ወጣቶች በቀላሉ የሚሰሩትን ጥሬ ጨው የማምረት ሥራ ላይ የሚሰማራ ባለሃብት ካለ በመንግስት የማስተካከል ሥራ እንደሚሰራ አመልክተዋል።
የአፋር ክልል ርዕሰ መስተዳደር አቶ አወል አርባ በማዕድንም ሆነ ሌሎች ዘርፎች ጥሬ ሃብትንና እሴት የሚጨምሩ ፋብሪካዎችን አንድ ላይ ማገናኘት ከባድ መሆኑን ነው የገለጹት።
በአፍዴራ ጨው ጥሬ ሃብቱን ከፋብሪካው ማገናኘት መቻሉን ገልጸው ይህም የአገራዊ ለውጡ አንዱ አካል መሆኑን ገልጸዋል።
"በቀጣይም ባለሃብቶች ጨው ላይ እሴት ጨምረው ወደ ገበያው ሲገቡ እንቅፋት ሳይገጥማቸው ሰላማዊና ደህንነቱ የተጠበቀ ሥራ ማከናወን እንዲችሉ የክልሉ መንግስት ከጎናቸው ይቆማል" ብለዋል።
የአፋር ህዝብ በሀብቱ ማዘዝና በፍትሃዊነት የመጠቀም መብቱን ተነጥቆ መቆየቱን አቶ አወል አስታውሰው፣ ከለውጡ በኋላ በጨው ምርት የተሰማሩ ባለሃብቶች የአዳሪ ትምህርት ቤት በመገንባት ማህበራዊ ኃላፊነታቸውን በመወጣታቸው ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
የቲ.ቲ.አር. አዮዳይዝድ ጨው ማምረቻ ፋብሪካ ባለአክሲዮን አቶ አበባው ደስታ በበኩላቸው በክልሉ በቂ የሆነ የጥሬ ጨው አቅርቦት እንዳለ ገልጸዋል።
"በመሆኑን ባለሃብቶች ከምግብነት ባለፈ ለኢንዱስትሪ ግብዓት የሚሆን የጨው ምርት ላይ በመሰማራት ገበያውን ማሳደግና የወጣቶችን ተጠቃሚነት ማጎልበት ይገባል" ብለዋል።