የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የሶስትዮሽ ድርድር ነገ ይጀመራል - ኢዜአ አማርኛ
የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የሶስትዮሽ ድርድር ነገ ይጀመራል
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 16/2013 ( ኢዜአ) ተቋርጦ የቆየው የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የሶስትዮሽ ድርድር ነገ የሚጀመር መሆኑን የኢፌዴሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አረጋገጠ።
በአፍሪካ ህብረት አደራዳሪነት ሲካሄድ የቆየው የሕዳሴ ግድብ የሶስትዮሽ ድርድር ነሐሴ 22 ቀን 2012 ዓ.ም ከተካሄደው የበይነ መረብ ውይይት በኋላ መቋረጡ የሚታወስ ነው።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ እንዳሉት የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የሶስትዮሽ ድርድር ነገ ከሰዓት በኋላ መካሄድ ይጀምራል።
በድርድሩ ላይ የኢትዮጵያ፣ ሱዳንና ግብጽ የውሃ ጉዳይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች እንደሚሳተፉ ተናግረዋል።
የድርድር ሂደቱ የሶስቱ አገራት መሪዎች ባስቀመጡት አቅጣጫ መሰረት የሚካሄድ መሆኑንም አምባሳደር ዲና ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ በሶስትዮሽ ድርድሩ የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅምና መብት ባስከበረ መልኩ ድርድሯን ትቀጥላለችም ብለዋል።
የሶስትዮሽ ድርድሩ ስኬታማ እንዲሆን ኢትዮጵያ ፅኑ ፍላጎት እንዳላትም ቃል አቀባዩ ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ፣ ሱዳንና ግብጽ በአፍሪካ ህብረት አደራዳሪነት ከሐምሌ 2012 ዓ.ም ጀምሮ የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የሶስትዮሽ ድርድር እያደረጉ ይገኛሉ።
እስካሁን በተደረጉት ድርድሮች የደቡብ አፍሪካ፣ የአውሮፓ ህብረትና የአሜሪካ ተወካዮች እንዲሁም የአፍሪካ ኅብረት የወከላቸው ባለሙያዎች በታዛቢነት እየተሳተፉ መሆኑ ይታወቃል።
ለመጨረሻ ጊዜ ሶስቱ አገራት በነበራቸው ድርድር የአገራቱ ባለሙያዎች በሕዳሴ ግድብ አሞላል እና ውሃ አለቃቀቅ ደንብ ላይ ሲከናወን የነበረው የባለሙያዎች ድርድር ሪፖርት ቀርቦ ውይይት እንደተደረገበት የሚታወስ ነው።
በድርድሩ በቀጣይ የሚኖረውን ሂደት በሚመለከት አገራቱ የድርድሩን ሂደት የሚገልጽ ደብዳቤ ለደቡብ አፍሪካዋ ዓለም አቀፍ ግንኙነትና ትብብር ሚኒስትር እና የአፍሪካ ኅብረት የአስፈጻሚ ምክር ቤት የወቅቱ ሊቀመንበር ዶክተር ናዴሊ ፓንዶር ለመላክ መስማማታቸው አይዘነጋም።
በወቅቱ ሱዳን የምትሰጠው ማረጋገጫ የሚጠበቅ ሆኖ የሦስትዮሽ ድርድሩ መስከረም 4 ቀን 2013 ዓ.ም ይቀጥላል ተብሎ የነበረ ቢሆንም እስካሁን ሳይካሄድ ቆይቷል።
የግድቡ የሶስትዮሽ ድርድር የተቋረጠው በሱዳንና በግብጽ ምክንያት እንደሆነ ኢትዮጵያ ይፋ ማድረጓ ይታወቃል።