ቀጥታ፡

የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ጉዞን ለማሳካት የሚያስችሉ መሰረታዊ መደላድሎች እንዲፈጠሩ እየተደረገ ነው -- ሚኒስቴሩ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 16/2013 ( ኢዜአ) በኢትዮጵያ የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ጉዞን ለማሳካት የሚያስችሉ መሰረታዊ መደላድሎችን የመፍጠር ሥራ እየተከናወነ መሆኑን የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር አስታወቀ።

የሚኒስትሮች ምክር ቤት በሰኔ ወር 2012 ዓ.ም ባደረገው መደበኛ ስብሰባ የኢትዮጵያ ዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ስትራቴጂ ወደ ሥራ እንዲገባ ማድረጉ የሚታወስ ነው።

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር አህመዲን መሐመድ ስትራቴጂው ኢትዮጵያ የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ጉዞ ውስጥ መሆኗን እንደሚያሳይ ለኢዜአ ገልጸዋል።

በስትራቴጂው አማካኝነት በአሁኑ ወቅት የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ጉዞውን ለማሳካት የሚያስችሉ መሰረታዊ መደላድሎችን የመፍጠር ሥራ እየተከናወነ መሆኑን ተናግረዋል።

በዚህም የዲጂታል ኢኮኖሚውን መሬት አውርዶ ለመስራት የሚያስችሉ የሕግ ማዕቀፎች ወደ ሥራ መግባት መጀመራቸውን ነው የገለጹት።

በተለይ ጀማሪ የንግድ አንቀሳቀሾች እና የፈጠራ ባለሙያዎች ለሚያመነጯቸው እውቀቶች የፋይናንስ ድጋፍ የሚያገኙበት አዋጅ ለዲጂታል ኢኮኖሚ ስርዓቱ ጉልህ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው አመልክተዋል።

አዋጁ እስከ ታህሳስ ወር 2013 ዓ.ም በህግ አውጪው አካል ጸድቆ ወደ ሥራ ይገባል ተብሎ እንደሚጠበቅም አመልክተዋል።

በአዋጁ አማካኝነት ጀማሪ የንግድ አንቀሳቃሾች በግልና በሽርክና መስራት እንዲችሉ ለሥራ የሚያስፈልጋቸውን ብድር የሚያገኙበት ሁኔታ እንደሚፈጥር ጠቁመዋል።

የኤሌክትሮኒክስ ግብይት አዋጁም ለዲጂታል ግብይት እድገት ምቹ ሁኔታ የሚፈጥር መሆኑንም ነው ዶክተር አህመዲን ያስረዱት።

"ለዲጂታል ትራንፎርሜሽን መሳካት ቁልፍ ሚና ካላቸው ጉዳዮች አንዱ የኢንተርኔት ግንኙነት አቅም (ኮኔክቲቪቲ) አንዱ ነው" ያሉት ዶክተር አህመዲን፣ የግሉ ዘርፍ ወደ ቴሌኮም ዘርፉ እንዲገቡ የሚያስችሉ ሥራዎች የዚሁ ዕቅድ አካል መሆናቸውን ተናግረዋል።

ከመሰረተ ልማት አኳያ እ.አ.አ ከ2007 ጀምሮ ወረዳዎችን በኤሌክትሮኒክስ ለማስተሳሰር ዓላማ ያደረገው ወረዳኔትን ጨምሮ ሌሎች የኤሌክትሮኒክስ ትስስር መንገዶችን የማስፋት ስራ እንደሚከናወን ተናግረዋል።

"የዲጂታል አገልግሎቱ የተሳለጠ እንዲሆን የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦትን ተደራሽነት ለማድረግ እየተሰራ ቢሆንም ብዙ ሥራዎችን ወደ ፊት መስራት ይጠይቃል" ብለዋል።

የዲጂታል ስርዓቱ ሲያድግ በዛው ልክ የሳይበር ጥቃቶች እያደጉ እንደሚመጡ ታሳቢ በማድረግ ኢትዮጵያ የሳይበር ደህንነት አቅሟን እንድታጎለብት የማድረግ ሥራ ከወዲሁ እየተከናወነ መሆኑንም ጠቁመዋል።

"በስትራቴጂው አብዛኛው የማህበረሰብ ክፍል በግብርና የሚተዳደር በመሆኑ ግብርናውን ማዘመንና በግብርና እሴት ሰንሰለቱ ያለ ደላላ ምርቱን ለገበያ ማድረስ የሚያስችል የዲጂታል ስርዓት የመዘርጋት ሥራ ይከናወናል" ብለዋል።

በቡና ግብይት የእሴት ሰንሰለት ውስጥ የቡና አምራቾች ምርታቸውን ለቡና ላኪዎች በዲጂታል ግብይት ስርዓት ተደራሽ የሚያደርጉበት ስርዓት ጨምሮ ሌሎች ስራዎች መጀመራቸውን ሚኒስቴር ዴኤታው በማሳያነት ጠቅሰዋል።

ዲጂታል ስርዓትን ያለ ዲጂታል እውቀት ማሰብ እንደማይቻል የገለጹት ዶክተር አህመዲን፣ ከዚህ አኳይ የዜጎችን የዲጂታል እውቀት ለማሳደግ ዘርፉን ወደ ትምህርት ስርዓት ውስጥ ማስገባት ጨምሮ ሌሎች ሥራዎች እየተከናወኑ መሆናቸውን አመልክተዋል።

የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ስትራቴጂ ከአገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ አጀንዳ የተወለደ ሀሳብ መሆኑንና ሁሉን አካታች የሆነ እድገት ለማምጣት የሚከናወነው ሥራ አካል መሆኑንም ተናግረዋል።

"ስትራቴጂውን እውን ለማድረግ የመፈጸም አቅምን፣ የቡድን ሥራና ጠንካራ የሥራ ባህልን ማሳደግ ከተቻለ መሳካት የማይችልበት ምንም ምክንያት የለም" ብለዋል ዶክተር አህመዲን ።

ኮቪድ -19 ወረርሽኝን ለመከላከል የተከናወኑ ሥራዎች የዲጂታል አሰራር ስርዓቶችን መተግበር አስፈላጊ እንድሆነ ያስተማረና ኢትዮጵያም ብዙ ተሞክሮዎችን ያገኝችበት መሆኑን ገልጸዋል።

ለዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ጉዞው ውጤታማነት የተቋማት ተናቦ መስራት በጣም አስፈላጊ እንደሆነና ባለድርሻ አካላት ከመንግስት ጋር በትብብር መስራት እንደሚገባቸው አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም