ቤተክርስቲያኗ ፕሬዚዳንት ትራምፕ በኢትዮጵያ ላይ ያስተላለፉትን ጦርነት የሚያጭር መልዕክት እንደምትቃወም ገለፀች - ኢዜአ አማርኛ
ቤተክርስቲያኗ ፕሬዚዳንት ትራምፕ በኢትዮጵያ ላይ ያስተላለፉትን ጦርነት የሚያጭር መልዕክት እንደምትቃወም ገለፀች
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 16/ 2013 ( ኢዜአ) የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ በኢትዮጵያ ላይ ያስተላለፉትን ጦርነት የሚያጭር መልዕክት እንደምትቃወም ገለጸች። ኢትዮጵያዊያን በግድቡ ላይ ያላቸውን የጋራ አቋም እንዲያጠናክሩም ጠይቀዋል።
የቤተክርስቲያኗ ቅዱስ ሲኖዶስ ፕሬዚዳንት ትራምፕ ከታላቁ ኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ጋር ተያይዞ ያስተላለፉትን ጦርነት የሚያጭር መልዕክት አስመልክቶ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥቷል።
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ፓትሪያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፕሬዚዳንቱ ግድቡን አስመልክተው ያስተላለፉትን መልዕክት አገሮችን የሚያጣላ በመሆኑ ቤተክርስቲያኗ ''አጥብቃ'' ትቃወመዋለች ብለዋል።
ፕሬዚዳንቱ በኢትዮጵያ ላይ ያስተላለፉት ተገቢ ያልሆነ መልዕከት ትዝብት ላይ የሚጥል መሆኑንም ተናግረዋል።
ፕሬዚዳንቱ ያሉትን ነገር የዓለም መንግሥታትና ሕዝቦች በጥልቀት እንዲገነዘቡት ቅዱስ ሲኖዶስ ጥሪውን ያስተላልፋል ብለዋል።
በአገር ውስጥና በውጭ አገራት የሚገኙ ኢትዮጵያዊያን እንዲሁም አገር የመምራት ኃላፊነት የተጣለባቸው የፌዴራልና የክልል መሪዎችም በግድቡ ጉዳይ በጋራ እንዲቆሙ ጠይቀዋል።
በተጨማሪም ተፎካካሪ ፓርቲዎች የፖለቲካ ልዩነቶቻቸውን በመተው ለአገር አንድነት በጋራ ሊቆሙ እንደሚገባም ፓትርያርኩ ጠቁመዋል።
''ኢትዮጵያዊያን እንደ ቀደሙት አባቶች በአንድነት፣ በመከባበርና በመመካከር መቆም ከቻሉ ከአቅማቸው በላይ የሚሆን ነገር እንደሌለም ከእኛ በላይ እድገታችንን የማይፈልጉ አካላት ሊገነዘቡት ይገባል'' ብለዋል።
ሲኖዶሱ "ኢትዮጵያ በእግዚአብሔርና በሕዝቦቿ አንድነት ተከብራና ተጠብቃ እንደምትኖር" እምነቱ መሆኑን ፓትርያርኩ አስታውቀዋል።