የህዳሴው ግድብ የሶስትዮሽ ድርድር ነገ እንደሚጀመር አፍሪካ ህብረት አስታወቀ

63

ጥቅምት 16/2013(ኢዜአ) በአፍሪካ ህብረት አደራዳሪነት ተጀምሮ ለተወሰኑ ጊዜያት ተቋርጦ የነበረው ደርድር ነገ እንደሚጀመር ህብረቱ አስታውቋል።

በኢትዮጵያ፣ በሱዳን እና በግብጽ መካከል ሲካሄድ የነበረው ደርድር እንደሚጀመር የገለጹት የወቅቱ የአፍሪካ ህብረት ሊቀመንበር የደቡብ አፍሪካው ፕሬዝዳንት ሲሪል ራማፎሳ ናቸው።

በሶስትዮሽ የድርድር መድረኩ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ አህመድ፣የሱዳኑ ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሃምዶክ እና የግብጽ ፕሬዝዳንት አል ሲ ሲ እንደሚገኙ ታውቋል።

የደቡብ አፍሪካው ፕሬዝዳንት ይህንን መግለጫ የሰጡት ከሰሞኑ የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ግብጽ የህዳሴው ግድብ ልታፈነዳው ትችላለች የሚል ንግግር ማድረጋቸውን ተከትሎ ስለመሆኑ ተገልጿል።

የደቡብ አፍሪካው ፕሬዝዳንት ሶስቱ ሀገራት በትብብር ፣ በቀና መንፈስ እና በሰጥቶ መቀበል መርህ ላይ በተመሰረተ መልኩ ሁሉንም የሚያግባባ ስምምነት ላይ ለመድረስ ዝግጁ እንደሆኑ ነው የገለጹት፡፡

በአፍሪካ ህብረት መሪነት በግድቡ ዙሪያ የሚካሄደው የሶስትዮሽ ድርድር መቀጠሉ ፤መሪዎች ለጉዳዩ ሰላማዊ እና የሚያግባባ መፍትሄ ለማምጣት ያላቸውን ጠንካራ ፖለቲካዊ ፍላጎት የሚያመለክት ነው ብለዋል፡፡

ፕሬዝዳንት ትራምፕ የሰጡት አወዛጋቢ መግለጫ በመላው ኢትዮጵያውያን እና የኢትዮጵያ ወዳጆች ዘንድ ቁጣን የቀሰቀሰ ሲሆን ተቀባይነት የሌለው ስለመሆኑም መንግስት ምላሽ መስጠቱ የሚታወስ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም