የክልል፣ የዞን እና የከተማ አስተዳደር መካከለኛ አመራሮች ስልጠና በአዲስ አበባ ተጀመረ

80

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 16/2013(ኢዜአ) በሰላም ሚኒስቴር የተዘጋጀው የክልል፣ የዞን እና የከተማ አስተዳደር መካከለኛ አመራሮች ስልጠና በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው።

ስልጠናው በአገሪቱ ለማሳደግ የታቀደው ሁሉን አሳታፊ የብሔራዊ ምክክር እና የሰላም ግንባታ ሂደት አካል ነው ተብሏል።

በስልጠናው ከሁሉም የአገሪቱ ክፍል የተወጣጡ የክልል፣ የዞን እና የከተማ አስተዳደር መካከለኛ አመራሮች ተገኝተዋል።

በስልጠናው መክፈቻ ላይ የተገኙት የሰላም ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ አቶ አለማየሁ እጅጉ በአገሪቱ የተጀመረው የለውጥ ሂደት በአዳዲስ እሳቤዎች፣ በሚታዩ እና በሚጨበጡ ድሎች የታጀበ መሆኑን ተናግረዋል።

የለውጥ ሂደቱ በሁሉም የአገሪቱ አካባቢዎች እንዲዳረስ እና የሚያጋጥሙ ተግዳሮቶችን በብልሀትና በመናበብ ማለፍ እንዲቻል ታስቦ ስልጠናው መዘጋጀቱን ገልጸዋል።

"ሚኒስቴሩ ሁለንተናዊ እና ዘላቂ ሰላም ለማረጋገጥ ዘርፍ ብዙ ሥራዎችን እየሰራ ይገኛል" ያሉት አቶ አለማየሁ፣ "ሰላም የሥራችን ሁሉ መነሻና መድረሻ ስለሆነ የሁሉንም ዜጋ ጥበቃ፣ ትኩረትና የነቃ ተሳትፎ ይጠይቃል" ብለዋል።

መድረኩ ዜጎች በነጻነት የሚነጋገሩበት፣ የመልካም አስተዳደር ችግሮች የሚለዩበት እንዲሁም ሀሳብ ከታችኛው የህብረተሰብ ክፍል ወደ ላይ የሚመጣበት ስለሆነ በመድረኩ የተገኙት በንቃት እንዲሳተፉ አስገንዝበዋል።

ስልጠናው ዛሬን ጨምሮ ለተከታታይ ሦስት ቀናት የሚካሄድ ሲሆን በቀጣይ ተመሳሳይ መድረኮች እንደሚዘጋጁም ታውቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም