ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ የጊምባ- ተንታ መገንጠያ የአስፓልት መንገድ ግንባታ አስጀመሩ - ኢዜአ አማርኛ
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ የጊምባ- ተንታ መገንጠያ የአስፓልት መንገድ ግንባታ አስጀመሩ
ባህርዳር፤ ጥቅምት 16/2013(ኢዜአ) በደቡብ ወሎ ዞን ከ2 ነጥብ 1 ቢሊየን ብር በላይ የሚካሄደው የጊምባ- ተንታ መገንጠያ የአስፓልት መንገድ ግንባታን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ዛሬ አስጀመሩ።
በመንገዱ ማስጀመሪያ ሥነ -ሥርዓት ከፍተኛ የፌደራልና የክልል ሥራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በወቅቱ የሚካሄዱ የመሰረተ ልማት ግንባታዎች በተያዘለቻው ጊዜ እንዲጠናቀቁ ህብረተሰቡ ድጋፍ ማድረግ እንዳለበት ተናግረዋል።
የአካባቢው አስተዳደር አካላትም በወሰን ማስከበር፣ የግንባታ ማምረቻ ቦታ በመስጠትና በሌሎች ተግባራት አስፈላጊውን ትብብር እንዲያደርጉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
በሚካሄዱ ዘርፈ ብዙ ልማቶች የብልጽግና ጉዞው እንዲሳካ አመራሩ፣ ባለሙያውና ሌሎች ባለድርሻ አካላት የተቀናጀ ጥረት ማድረግ እንዳለባቸው አሳስበዋል።
ህብረተሰቡም ለልማት ስራዎች ከሚያደርገው ድጋፍና ትብብር ባሻገር አንድነቱን ጠብቆ የአካባቢው ሰላም እንዲከበር ጥረት ማድረግ እንዳለበትም አመልክተዋል።
የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ኢንጅነር ሃብታሙ ተገኝ በበኩላቸው ከጊምባ - ተንታ መገንጠያ የሚገነባው የአስፓልት መንገድ 80 ኪሎ ሜትር ርዝመት እንዳለው አስታውቀዋል።
ለመንገዱ ግንባታም በፌደራል መንግስት ከ2 ነጥብ አንድ ቢሊየን ብር በላይ በጀት መመደቡን ጠቁመው፤ በ3 ዓመታት ውስጥ ይጠናቀቃል ተብሎ የሚጠበቅ መሆኑን ገልጸዋል።
የአስፓልት መንገድ ግንባታው በተያዘለት ጊዜ በጥራት ተገንብቶ እንዲጠናቀቅም ባለስልጣኑ አስፈላጊውን ክትትልና ቁጥጥር እንደሚያደርግ አረጋግጠዋል።
ዛሬ የተጀመረው የጊምባ- ተንታ መገንጠያ መንገድ የአስፓልት መንገድ ግንባታ ከአዲስ ዓለም-ጋሸና-ላሊበላ ሰቆጣ ያለው ሀገር አቋራጭ መንገድ አካል መሆኑ ተመልክቷል።