ቀጥታ፡

የፕሬዚዳንት ትራምፕ ንግግር የአሜሪካን ህዝብንም ሆነ ምክር ቤቶች ይወክላል የሚል እምነት የለኝም--የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት

ጥቅምት 15/2013 (ኢዜአ) የፕሬዚዳንት ትራምፕ ንግግር የአሜሪካን ህዝብንም ሆነ ምክር ቤቶች ይወክላል የሚል እምነት እንደሌለው የኢፌዴሪ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ገለጸ።

የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ንግግር ከግል ስሜት የመነጨ የግል ፍላጎትን የሚያንፀባርቅ እንጂ በማንኛውም መልኩ የአሜሪካን ህዝብንም ሆነ ምክር ቤቶች ይወክላል የሚል እምነት እንደሌለው የኢፌዴሪ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ገለጸ።

ፕሬዚዳንት ትራምፕ የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን አስመልክተው ያስተላለፉት መልእክት ኃላፊነት የጎደለው የአሜሪካ መንግስትንም ሆነ ህዝብ የማይመጥን እንደሆነም ምክር ቤቱ ገልጿል።

እንዲህ አይነቱ ኃላፊነት የጎደለው የማንአለብኝነት አነጋገር ከአንድ ለዴሞክራሲ፣ ለእኩልነት እና ለፍትህ እቆማለሁ ከምትል አገር ፕሬዚዳንት ሲሰማ ደግሞ እጅግ አሳዛኝና አሳፋሪ እንደሆነ ምክር ቤቱ ጠቅሷል።

‘’ታላቁ የህዳሴ ግድባችንን ከፍፃሜ ከማድረስ ለአፍታም ያህል የሚያቆመን አይኖርም’’ ያለው ምክር ቤቱ፤ የረዥም ግዜ ጥሩ ወዳጅ የሆኑት ኢትዮጵያና አሜሪካ መንግሥታት ጠንካራ ስትራቴጂካዊ ትብብርና ወዳጅነት እንዳላቸው አውስቷል።

‘’ይህ ግንኙነትና ትብብር ወደፊትም ተጠናክሮ ይቀጥላል’’ ብሏል።

“ለእኛ ለኢትዮጵያዊያን የህዳሴው ግድባችን የማንነታችን አርማ፣ የአንድነታችን መገለጫ እና የቃል ኪዳናችን ህያው ሐውልት ነው” ሲል ገልጿል።

“ባሳለፍነው የጋራ ታሪካችን የቀኝ ገዢዎችን ፍላጎት እና በተደጋጋሚ ከውጭ ወራሪ ኃይሎች የተቃጣብንን የወረራ ጥቃት በአንድነት ቆመን በተባበረ ክንድ እንዳከሸፍን ሁሉ ከውስጥ እና ከውጭ በየጊዜዉ የሚያጋጥሙንን ጥቃቶችና ሴራዎች እንደወትሮው ሁሉ በአንድነት ተቋቁመንና መክተን ታላቁን የህዳሴ ግድባችንን ከፍፃሜ ማድረስ ይኖርብናል” ሲል ምክር ቤቱ መልዕክቱን አስተላልፏል።

ለኢትዮጵያዊያን በአሁኑ ወቅት በአንድነት መቆም የህልውናና የሉዓላዊነት ጉዳይ እንደሆነም አመልክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም