ኢጋድ በሕዳሴው ግድብ ዙሪያ ውይይቶችን እንደ ሚያበረታታ አስታወቀ - ኢዜአ አማርኛ
ኢጋድ በሕዳሴው ግድብ ዙሪያ ውይይቶችን እንደ ሚያበረታታ አስታወቀ
አዲስ አበባ ፣ ጥቅምት 15/2013 ( ኢዜአ) በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ጉዳይ ውይይቶችን እንደሚያበረታታ የምስራቅ አፍሪካ የልማት በየነ መንግስታት (ኢጋድ) አስታወቀ።
ኢጋድ ዛሬ ባወጣው መገለጫ ላይ በግድቡ ዙሪያ የሚደረጉ ምክክሮችና ውይይቶች እንዲቀጥሉ መክሯል።
የኢጋድ ዋና ጸሐፊ ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ የሕዳሴ ግድብን አስመልክቶ በኢትዮጵያ፣ ሱዳንና ግብጽ መካከል ሲካሄድ የቆየው ድርድር ዘላቂ መፍትሄ እንዲያመጣ ውይይቶችና የመፍትሄ ሃሳቦች መቀጠል እንዳለባቸው መክረዋል።
በዓባይ ወንዝ እኩል ተጠቃሚነት ላይ ከስምምነት ለመድረስ ከተፈለገ ለድርድር መዘጋጀትና መንገዱን ማመቻቸት ለሁሉም አገራት ብቸኛው መፍትሄ መሆኑን በአጽኖት ገልጸዋል።
"የቀጠናውን ሰላምና መረጋጋት ሊያደፈርሱ ከሚችሉ ጉዳዮች በመራቅ ለሰላምና መረጋጋት መስፈን ትኩረት መስጠት ይገባል" ብለዋል።
ጎረቤት አገሮች የሚጋሯቸውን የጋራ እሴትና ታሪኮች ማጠናከር እንዳለባቸውም ነው የገለጹት።
በአፍሪካ ሕብረት እየተመራ የሚካሄደው የሦስቱ አገራት ድርድር መፍትሄ እንደሚያመጣ በኢጋድ በኩል እምነት መኖሩንም ነው የተናገሩት።
ዋና ጸሐፊው ዶክተር ወርቅነህ ምክንያታዊነት ለሁሉም ተጠቃሚነት አሸናፊ እንደሚያደርግ ያላቸውን ጽኑ እምነትም ገልጸዋል።