ቀጥታ፡

ከሃይቅ ቢስቲማ-ጭፍራ 74 ኪሎ ሜትር የአስፋልት መንገድ ግንባታ ተጀመረ

ደሴ ጥቅምት 15/2013 (ኢዜአ) በደቡብ ወሎ ዞን ከሃይቅ ቢስቲማ-ጭፍራ 74 ኪሎ ሜትር የአስፋልት መንገድ ግንባታ ዛሬ መጀመሩን የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን አስታወቀ። 

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አቢይ አህመድን ጨምሮ የፌዴራልና የክልል ከፍተኛ ባለስልጣናት በመንገድ መስጀመሪያ ስነ-ስርዓቱ ላይ ተገኝተዋል።

የባለስልጣኑ ዋና ደይሬክተር ኢንጂነር ሃብታሙ ተገኝ በስነ ስርዓቱ ላይ እንዳሉት የመንገድ መሰረተ ልማት መጠናከር የከተማውንና የገጠሩን ማህበረሰብ ለማስተሳስር የሚያስችል ነው።

"ከሃይቅ ቢስቲማ-ጭፍራ የሚገነባው የአስፋልት መንገድም 74 ኪሎ ሜትር የሚሸፍን ሲሆን ከ2 ነጥብ 1 ቢሊየን ብር በላይ ወጭ ይደረግበታል" ብለዋል።

በአራት ዓመታት ውስጥ ይጠናቀቃል ተብሎ የታቀደው የመንገድ ፕሮጀክት ለዘመናት ሲነሳ የነበረውን የህዝብ የልማት ጥያቄ የሚመልስ አንደሆነም አስረድተዋል።

ከሃይቅ ቢስቲማ-ጭፍራ የአስፋልት መንገድ ግንባታም የአካባቢውን ማህበረሰብ ከአፋር ክልል ጋር በማስተሳሰር የጋራ ተጠቃሚነትን የሚያሳድግ መሆኑንም ገልጸዋል።

የግንባታው ተቋራጭ ፓወር ኮን ሃላፊነቱ የተወሰነ የግል ድርጅት ስራ አስኪያጅ ኢንጂነር አፈወርቅ በለጠ እንዳሉት የመንገድ ግንባታውን በተያዘለት ጊዜ ለማጠናቀቅ በቁርጠኝነት የሚሰራ ይሆናል።

ምንም እንኳ የአካባቢው መልክዓ ምድራዊ አቀማመጥ አስቸጋሪ ቢሆንም ችግሩን ተቋቋሞ መንገዱን በጥራት ለመገንባት የሚያግዳቸው ነገር እንደሌለም ተናግረዋል።

የአካባቢው መስተዳድርና ህዝቡ በወሰን ማስከበርና ለመንገድ ግንባታው የሚውል የቁሳቁስ ማምረቻ ቦታ በመስጠት አስፈላጊውን ትብብር እንዲያደርግላቸው መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም