ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ ከ92 ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን በላይ በካይ ጋዝ መቀነስ ችላለች--ኮሚሽኑ

አዳማ፣ ጥቅምት 15/2013 (ኢዜአ) ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥ የሚቋቋም የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ግንባታ ስትራቴጂ መተግበር ከጀመረች ጀምሮ ከ92 ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን በላይ በካይ ጋዝ መቀነስ መቻሏን የአካባቢ ደንና አየር ንብረት ለውጥ ኮሚሽን አስታወቀ።

ኮሚሽኑ ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር አረንጓዴ ኢኮኖሚ ትግበራ የሚኒስትሮች ስትሪንግ ኮሚቴ ጋር በዘርፍ የተከናወኑና የተገኙ ለውጦችን ዛሬ በቢሾፍቱ ከተማ ገምግሟል።

የአካባቢ ደንና አየር ንብረት ለውጥ ኮሚሽነር ፕሮፌሰር ፍቃዱ በየነ በወቅቱ እንደገለፁት የአየር ንብረት ለውጥ በኢኮኖሚ፣ በማህበራዊና በምጣኔ ሀብት ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ እየፈጠረ ነው።

በዝናብ ጥገኝነት ላይ የተመሰረተ የግብርና ልማትና ምርታማነት ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ እያሳደረ መሆኑን ጠቅሰዋል ።

ባለፍት አስር ዓመታት በፌዴራልና በክልል ደረጃ የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ግንባታ ስትራቴጂና የማስፈፀሚያ ስልቶችን በመቅረፅ ተግባራዊ ሲደረግ መቆየቱን አስታውሰዋል ።

በትግበራ ሂደቱ ከግብርና፣ ትራንስፖርት፣ ከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሴክተር ወደ አካባቢ አየር የሚለቀቅ ከ92 ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን በላይ በካይ ጋዝ  ማስቀረት መቻሉን ኮሚሽነሩ ተናግረዋል።

ከ2003 ዓ.ም ጀምሮ በእቅድ ከተቀመጠው የበካይ ጋዝ ቅነሳ አቅጣጫ አኳያ ተስፋ ሰጭ አፈፃፀም የታየበት ቢሆንም የተፈለገው ውጤት ላይ መድረስ አለመቻሉን ጠቁመዋል ።

እንደ ፕሮፌሰር ፍቃዱ ገለጻ የመድረኩ ዋና ዓላማ በቀጣይ አስር ዓመት የበካይ ጋዝ ልቀትን ዜሮ ለማድረስ ሁሉም የፌዴራልና የክልሎች የማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ሴክተሮች ዋና የልማት ዕቅዳቸው አካል አድርገው በማካተት እንዲተገብሩት ማስቻል ነው ።

በተለይ ታዳሽና አማራጭ የኃይል አቅርቦት፣ የልማት ፕሮጀክቶችና የኢንቨስትመንት ተቋማት የማህበረሰብና አካባቢያዊ ተፅዕኖ ግምገማ በአረንጓዴ አሻራ ፕሮግራም መሪ ዕቅድ ልዩ ትኩረት ያገኙ መሆኑን ገልጸዋል።

ኮሚቴው በስትራቴጂው አፈፃፀምና ስልት ላይ ድጋፍ ከማድረግ ባለፈ የተቀናጀ ትግበራ እንዲኖረው ክትትል ማድረግ እንደሚገባው ኮሚሽነሩ አስገንዝበዋል ።

ባለፍት አስር ዓመታት 150 ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን ሙቀት አማቂ ጋዞችን ለመቀነስ የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ግንባታ ትግበራ የተጀመረ ቢሆንም ለማሳካት የተቻለው 92 ነጥብ 6 ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን ብቻ ነው" ያሉት ደግሞ በኮሚሽኑ የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖ ቅነሳ ዳይሬክተር አቶ ሰይድ ደሴ ናቸው።

"ሙቀት አማቂ ጋዞችን ለመቀነስ የአረንጓዴ ልማት ስትራቴጂን መተግበር፣ የልማት ስራዎችን በቴክኖሎጂ መደገፍና ማዘመን፣ የማህበራዊ አገልግሎቶችን በዘመናዊ ቴክኖሎጂ እንዲቃኙ ማስቻል የዕቅድ ማስፈፀሚያ ስልቶች ናቸው" ብለዋል።

በ2022 ዓ.ም 64 በመቶ የካርበን ልቀት ለመቀነስ ግብ መቀመጡን አመላክተዋል።

ኢትዮጵያ  ከምታመነጨው 400 ሚሊዬን ሜትሪክ ቶን ሙቀት አማቂ ጋዞች ውስጥ 250 ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን ለመቀነስ መታቀዱንም ዳይሬክተሩ ገልጸዋል።

በአሁኑ ወቅት በግብርና፣ ደን ልማትና ጥበቃ እንዲሁም በአረንጓዴ አሻራ መርሀ ግብር መልካም ውጤት እየታየባቸው መሆኑን ጠቅሰዋል ።

በትራንስፖርት፣ ከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሴክተሮች፣ በልማት ፕሮጀክቶችና ኢንቨስትመንት ተቋማት ላይ በሙሉ አቅም መስራት  እንደሚገባ አስገንዝበዋል ።

በዘርፉ የቴክኖሎጂ አቅምና ዲጅታል አገልግሎት ከማስፋት ጀምሮ 18 የሚተገበሩ አማራጮች መዘጋጀታቸውን ዳይሬክተሩ አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም