አገርና ሕዝብን ከማንኛውም አደጋ መከላከል የሚያስችል ወታደራዊ አቅም አለን -- ጄኔራል ብርሃኑ ጁላ - ኢዜአ አማርኛ
አገርና ሕዝብን ከማንኛውም አደጋ መከላከል የሚያስችል ወታደራዊ አቅም አለን -- ጄኔራል ብርሃኑ ጁላ
አዲስ አበባ ፣ ጥቅምት 15/2013 (ኢዜአ) ሀገርና ሕዝብን ከማንኛውም የውስጥና የውጭ አደጋ መከላከል የሚያስችል ሙሉ ወታደራዊ አቅም መኖሩን የጦር ኃይሎች ምክትል ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ጄኔራል ብርሃኑ ጁላ ተናገሩ።
ምክትል ጠቅላይ ኢታማዦር ሹሙ ይህንን የተናገሩት የመከላከያ ሠራዊት የልዩ ዘመቻዎች ኃይል ማዘዣ በአምስት ሻለቃ ያሰለጠናቸውን የኮማንዶ አባላት በብላቴ የጦር ማሰልጠኛ ማዕከል ባስመረቀበት ወቅት ነው።
ጄኔራል ብርሃኑ በተለይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በሀገርና በሕዝብ ላይ ብጥብጥና ትርምስ ለመፍጠር እየሰሩ ያሉ አካላት መኖራቸውን ጠቅሰው፤ ሠራዊቱ የሚጠነሰሰውን ሴራ የመመከት ሙሉ አቅም እንዳለው አስታውቀዋል።
ምሩቃን የኮማንዶ አባላትም በስልጠናው ያገኙትን እውቀትና ክህሎት ወደ ተግባር በመቀየር ሀገሪቱ ሊያጋጥሟት ከሚችሉ ማንኛውም አደጋ መጠበቅ እንዳለባቸውም አሳስበዋል።
"ሀገሪቱ በውጭ እና በውስጥ የጥፋት ኃይሎች ሊገጥማት የሚችለውን አደጋ መመከት የሚያስችል ስልጠና፣ ትጥቅና የተሟላ አቅም አለን" መኖሩንም ምክትል ጠቅላይ ኢታማዦር ሹሙ አስረድተዋል።
እነዚህ የሽብር አካላት አንዱ ብሔር በሌላው ላይ እንዲነሳና ብጥብጥ እንዲፈጠር ለማድረግ ባለፉት ሁለት ዓመታት ከሃያ በላይ ሁከቶችን መፍጠራቸውንም ጄኔራል ብርሃኑ ገልጸዋል።
የጸጥታ ኃይሉ ከህዝብ ጋር በመሆን ሁሉንም ሁከቶች ማምከን መቻሉንም ተናግረዋል።
እነዚህ የጥፋት ኃይሎች ሰሞኑንም በቤንች ሸኮ ዞን ጉራፈርዳ ወረዳ ይህንኑ ተግባር እየፈጸሙ መሆናቸውን ጠቅሰው፤ ተግባሩን የሚፈጽሙት ከኢትዮጵያዊያን ግጭት ጥቅም ከሚያገኙ አካላት ጋር በማበር መሆኑን ጠቁመዋል።
"ይሁን እንጂ ይህ ተግባር አይቀጥልም፤ በሠራዊቱና በሕዝቡ የጋራ ሥራ እናመክነዋለን" ነው ያሉት ምክትል ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ጄኔራል ብርሃኑ ጁላ።
የመከላከያ ሠራዊቱን ዘለቄታዊ በሆነ መንገድና የሀገሪቱን ሉዓላዊነት በሚያስከብር መልኩ አጠናክሮ የማደራጀት ሥራ እንደሚሰራም አመልክተዋል።