ቀጥታ፡

የፕሬዝዳንት ትራምፕ ንግግር የሃገራችንን ሉአላዊ መብት የዘነጋ ነው -- ምሁራን

አዳማ፣ ጥቅምት 15/2013 (ኢዜአ) የፕሬዝዳንት ትራምፕ ንግግር የ የኢትዮጵያ በተፈጥሮ ሃብቷ የመጠቀም መብት የዘነጋና ወገንተኛነት የተሞላበት መሆኑን ምሁራን ገለጹ።

አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ የአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ምሁራን እንደተናገሩት የፕሬዝዳንቱ ንግግር ከታላቋ የአሜሪካ የሚጠበቅ አይደለም፤ ንግግሩ በግድቡ ዙሪያ የሁለቱን ሀገራት መንግስታትም ሆነ ህዝቦችን ወደ ግጭት የሚያስገባ አይደለም።

በዩኒቨርሲቲው የአካዳሚክ ጉዳዮች ፕሬዝዳንት ዶክተር ተሾመ አብዶ እንደገለፁት የፕሬዝዳንቱ ንግግር የኢትዮጵያን በሃብቷ የመጠቀም ሉዓላዊ መብት የዘነጋ ከመሆኑም ባለፈ የአንድ ሀገር መሪን የማይመጥን ነው።

በግድቡ ዙሪያ ለግብጽ ሱዳንና ኢትዮጵያ ብቸኛውና ጠቃሚ መፍትሄ  መነጋገርና ሁሉንም ባማከለ መልኩ ከስምምነት መድረስ እንጂ የሶስተኛ ወገን ግጭት ቀስቃሽ ንግግር እንዳልሆነም ተናግረዋል።

የፕሬዝዳንቱ ንግግር አሜሪካ የራሷን ጥቅም በውጭው ዓለም ለማስጠበቅ የምታደርገው ጥረት አካል እንደሆነ የገለጹት ምሁሩ፤  "በህዳሴው ግድብ ዙሪያ የጋራ ተጠቃሚነትን ያረጋገጠ ካልሆነ በስተቀር ወገንተኝነት የተሞለበት ንግግር ትርጉም አልባ ነው" ብለዋል።

ግብፅ በፕሬዝዳንቱ ንግግር ተነሳስታ ግጭት ውስጥ ትገባለች ብለው እንደማያስቡ የገለጹት ዶክተር ተሾመ፤ "ጥቅም ከማይገኝበት ትንኮሳ ይልቅ በድርድርና በመነጋገር ተማምኖ ሁሉም አሸናፊ የሚሆንበት አማራጭ ይበጃል" ብለዋል።

አሜሪካ አሁን ላለችበት የምርጫና የፖለቲካ ሁኔታ የህዳሴ ግድብ ጉዳይ መነሳቱ ፕሬዝዳንቱን አሸናፊ እንደማያደርጋቸው የተናገሩት ደግሞ የዩኒቨርሲቲው የጥናትና ምርምር ዘርፍ ፕሬዝዳንት ዶክተር ሽፈራው ፈይሳ ናቸው።

ፕሬዝዳንት ትራምፕ ግብፅ የህዳሴን ግድብ ልታፈነዳ ትችላለች ማለታቸው ግብፅን በንግግር ከማስደሰት ባለፈ ምንም ውጤት እንደማይኖረው ተናግረዋል።

"አሁን ግድቡን መንካት በራስ መቀለድ ነው ግብፅም ብትሆን የሚጠቅማት የሶስተኛ ወገን ግጭት ቀስቃሽነትና ጣልቃ ገብነት ሳይሆን ከጉዳዩ ባለቤቶች ጋር መነጋገርና በግድቡ የጋራ ተጠቃሚ መሆን ነው" ብለዋል።

የፕሬዝዳንቱ ንግግር ኃላፊነታቸውን የማይመጥንና ያልተገባ እንደሆነ የገለጹት ዶክተር ሽፈራው፤ ከዚህ ይልቅ አሜሪካ ሀገራቱን በማቀራረብ ሁሉም አሸናፊ የሚሆንበትን ምቹ ሁኔታ ብትፈጥር መልካም እንደነበረ አስረድተዋል።

አሁንም የኢትዮጵያ ህዝብ እንደ ወትሮው ሁሉ በአንድነት የግድቡን ግንባታ በማጠናቀቅ ዳግም ታሪክ መስራት እንደሚጠበቅበት ምሁራኑ አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም