ለመገናኛ ብዙሃን በማዕከል መረጃ የሚሰጥበት ተቋማዊ አሰራር ዳግም መመለስ አለበት --የህዝብ ዕንባ ጠባቂ - ኢዜአ አማርኛ
ለመገናኛ ብዙሃን በማዕከል መረጃ የሚሰጥበት ተቋማዊ አሰራር ዳግም መመለስ አለበት --የህዝብ ዕንባ ጠባቂ
አዲስ አበባ ፣ ጥቅምት 15/2013 ( ኢዜአ) መንግስት ለመገናኛ ብዙሃን በማዕከል መረጃ የሚሰጥበትን ተቋማዊ አሰራር ዳግም መመለስ እንደሚገባው የኢትዮጵያ የህዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም አስታወቀ።
ለመገናኛ ብዙሃን በማዕከል ደረጃ መግለጫዎችና መረጃዎችን ይሰጥ የነበረው የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት በ2011 ዓ.ም መፍረሱ የሚታወስ ነው።
የኢትዮጵያ የህዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም ዋና ዕንባ ጠባቂ ዶክተር እንዳለ ኃይሌ መገናኛ ብዙሃን መረጃ የማግኘት መብታቸው የተጠበቀ እንዲሆን መረጃ የሚያገኙበት ተቋማዊ አደረጃጀት መኖር እንዳለበት ለኢዜአ ገልጸዋል።
በዚህ ረገድ ቀደም ሲል የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ለመገናኛ ብዙሃን በማዕከል ደረጃ መረጃዎችን ሲሰጥ ቢቆይም ተቋሙ ከፈረሰ በኋላ መረጃዎችን ለማግኘት ፈታኝና አስቸጋሪ እየሆነባቸው መምጣቱን ተናግረዋል።
ከመንግስት ጋር በተደረጉ ውይይቶች ሁሉም ተቋማት መረጃዎችን ለመገናኛ ብዙሃን የመስጠት ግዴታ እንዳለባቸው አቅጣጫ ቢቀመጥም ያልተማከለ መረጃ አሰጣጥ ችግር እየፈጠረ ስለመሆኑ መገለጹን አመልክተዋል።
የችግሩ ዘላቂ መፍትሄም መንግስት ለመገናኛ ብዙሃን በማዕከል መረጃ የሚሰጥበትን ተቋማዊ አሰራር ዳግም መመለስ ሲችል መሆኑን ዶክተር እንዳለ አመልክተዋል።
"በተለያዩ ተቋማት ውስጥ የሚገኙ የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያዎችን ሙያዊ ክህሎት በተላበሰ መልኩ እንዲሰሩ ማድረግም ይገባል" ብለዋል ዶክተር እንዳለ፡፡
ከዚህ ባለፈ መረጃ የመስጠት ዋነኛ ኃላፊነት የእነርሱ መሆኑን ማስገንዘብ እንደሚገባም ነው ያመለከቱት።
የመንግስት ሥራ አስፈጻሚዎች የሚፈልጉትን መረጃ ብቻ ሳይሆን መገናኛ ብዙሃን እና ማህበረሰቡ የሚፈልጓቸውን መረጃዎችንም መስጠት እንዳለባቸው ተናግረዋል።
"የመገናኛ ብዙሃንና የመረጃ ነጻነት አዋጅ ቁጥር 590/ 2000 መገናኛ ብዙሃን የተዛባ መረጃ ሲያቀርቡ ተጠያቂ የሚያደርግበት አሰራር አለው" ያሉት ዶክተር እንዳለ፤ አዋጁ መረጃ የሚከለክሉ አካላትን ተጠያቂ እንደማያደርግ ተናግረዋል።
በተጨማሪም በአዋጁ ላይ መገናኛ ብዙሃን መረጃ ተከለከልን ለማለት መረጃ የጠየቁትን አካል 10 ቀን መጠበቅ እንዳለባቸው የተቀመጠ ሲሆን ይሄም ወቅታዊ መረጃ እንዳያገኙ እያደረጋቸው መሆኑን ገልጸዋል።
"በተለያየ ጊዜ በኢትዮጵያ ተነስተው በነበሩ ግጭቶችና አለመረጋጋቶች ወቅት መገናኛ ብዙሃን መረጃ ለማግኘት እንደሚቸገሩ በመተከል የነበረው የጸጥታ ችግር አንድ ማሳያ ነው" ብለዋል ዋና ዕንባ ጠባቂ ዶክተር እንዳለ።
እንደ ዶክተር እንዳለ ገለጻ መንግስት በወቅቱ መረጃዎችን አለመስጠቱ መገናኛ ብዙሃንና ህብረተሰቡ ሐሰተኛ መረጃዎችን እንደ ትክክለኛ መረጃ እንዲወስዱ በር የሚከፍት ነው።
መገናኛ ብዙሃን መረጃዎች ሲከለከሉ ቅሬታቸውን ለዕንባ ጠባቂ ተቋም ማቅረብ የሚችሉበት አሰራር ቢኖርም እስካሁን መረጃ ተከልክያለሁ ብሎ በይፋ አቤቱታ ያቀረበ መገናኛ ብዙሃን አለመኖሩን ገልጸዋል።
የዕንባ ጠባቂ ተቋም መረጃ አልሰጠኝም ብሎ ቅሬታ ላቀረበ መገናኛ ብዙሃን በተሰጠው ስልጣን አማካኝነት መረጃ ያልሰጠውን አካል የማጋለጥ ሥራ እንደሚያከናውንም አመልክተዋል።
በመገናኛ ብዙሃን በኩልም የአንድ ወገን መረጃ ይዘው ተገቢውን ማጣራትና ጥረት ሳያደርጉ ሌላኛው አካል መረጃ ለመስጠት ፈቃደኛ አይደለም በሚል የሚያወጡት ዘገባ ሚዛናዊት እንደሚጎለው ነው የተናገሩት።
መገናኛ ብዙሃን በተቻላቸው መጠን ለህብረተሰቡ ሚዛናዊና ትክክለኛ መረጃ መስጠት እንደሚገባቸው ነው ዶክተር እንዳለ ያስረዱት።
መረጃ የሚከለክሉ አካላት በሕግ የሚጠየቁበትን አሰራር መዘርጋትና መረጃ የማግኘት መብት ለዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ ያለውን አስተዋጽኦ የሚረዳ ማህበረሰብ መፍጠር እንደሚገባና ይህም የአመለካከት ለውጥ እንደሚጠይቅ አስረድተዋል።