የአሜሪካው ፕሬዝዳንት በሕዳሴ ግድብ ላይ የሰጡት አስተያያት ''ኃላፊነት የጎደለው ነው''- የኢትዮጵያ ተደራዳሪዎች - ኢዜአ አማርኛ
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት በሕዳሴ ግድብ ላይ የሰጡት አስተያያት ''ኃላፊነት የጎደለው ነው''- የኢትዮጵያ ተደራዳሪዎች
አዲስ አበባ ጥቅምት 14/2013 (ኢዜአ) - የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ላይ የሰጡት አስተያየት ''ኃላፊነት የጎደለው ነው'' ሲሉ የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ተደራዳሪዎች ተናገሩ።
ተደራዳሪዎቹ ዶክተር ያዕቆብ አርሳኖና አምባሳደር ኢብራሂም ኢድሪስ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ፕሬዝዳንቱ ግድቡን አስመልክተው የሰነዘሩት አስተያየት ''ኃላፊነት የጎደለው'' ብለውታል።
የግድቡ ተደራዳሪና የአባይ ውኃ ጉዳይ ተመራማሪው ዶክተር ያዕቆብ አርሳኖ ፕሬዝዳንት ትራምፕ የሰጡት አስተያየት በኢትዮጵያና በአሜሪካ መንግሥታት እንዲሁም በሁለቱ አገሮች ሕዝቦች መካከል ለዘመናት የቆየውን የረጅም ጊዜ ጠንካራ ትብብር ከግምት ውስጥ ያላስገባ መሆኑን ገልጸዋል።
"ግብፅ በኢትዮጵያ ጦርነት እንድታውጅ ድጋፍ የሚያደርግ ንግግር ማድረግ የማይጠበቅ ኃላፊነት የጎደለውና የማይቻል ነው" ብለዋል።
የኢትዮጵያ አጋሮች፣ የአሜሪካ የኮንግረስ አባላትና በአሜሪካ የሚገኘው የኢትዮጵያ ማኅበረሰብ ንግግሩ ''በጠንካራ ሁኔታ'' እንዲያወግዙት ዶክተር ያዕቆብ ጠይቀዋል።
"የተለያዩ አካላት በኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅሞች እጃቸውን ሲያስገቡ ይሄን በፍጹም የማንፈቅደውና የማንቀበለው ነው የሚል ሕዝባዊ ተሳትፎና አንድነት ያስፈልጋል። ለዚህም ኢትዮጵያውያንም ለመብቶቻቸው መጠበቅ በፅናት በጋራ መቆም ይገባቸዋል" ሲሉም ተናግረዋል።
የቀድሞ በግብፅ የኢትዮጵያ አምባሳደርና የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ተደራዳሪ አምባሳደር ኢብራሂም ኢድሪስ በበኩላቸው የአሜሪካው ፕሬዝዳንት በግድቡ ዙሪያ የሰጡት አስተያያት በግላቸው እንደያዙት አቋም ሊታይ እንደሚገባና የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲና የአብዛኛውን የአሜሪካ ምክር ቤት አባላት አይወክልም ብለዋል።
ኢትዮጵያና አሜሪካ ጠንካራ ትብብር እንዳላቸው አስታውሰው፣ የአንዲት አገር ሉዓላዊነት በመዳፈር ጦርነት ማወጅ ተገቢ እንዳልሆነ ገልጸዋል።
''ኢትዮጵያውያን የትኛውንም ዋጋ ከፍለን የአገራቸውን ሉዓላዊነት ለመጠበቅ ወደኋላ አይሉም። ይሄንንም ታሪክ ይነግረናል" በማለት አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።