ቀጥታ፡

ጊዜው የግድቡ የሦስትዮሽ ድርድር ተግባራዊ ምላሽ መስጫ እንጂ ውጥረቶችን መጨመሪያ አይደለም-የአውሮፓ ኅብረት

አዲስ አበባ ጥቅምት 14/2013 (ኢዜአ) "ጊዜው በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የሦስትዮሽ ድርድር መፍትሔ እንዲገኝ ተግባራዊ ምላሽ መስጫ እንጂ ውጥረቶችን መጨመሪያ አይደለም" ሲሉ የአውሮፓ ኅብረት ኮሚሽን ምክትል ፕሬዝዳንት ጆሴፍ ቦሬል ገለጹ።

በናይል ተፋሰስ ውስጥ የሚገኙ ከ250 ሚሊዮን በላይ ዜጎች ከታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የውኃ ሙሌትን አስመልክቶ በሚካሄደው የሦስትዮሽ ድርድር ከሚደረሰው ሥምምነት ተጠቃሚ ለመሆን እየተጠባበቁ መሆናቸውን ተናግረዋል።

በተጨማሪም ዜጎቹ በውኃ ደህንነት፣ በመስኖ፣ በግብርና ምርትና የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጨት መስኮች መዋዕለ ነዋይ እንዲፈስም ይጠባበቃሉ ብለዋል ሚስተር ቦሬል።

ኢትዮጵያ፣ ግብፅና ሱዳን በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ውኃ ሙሌት ሥምምነት ላይ መድረስ በእጃቸው ያለ ጉዳይ እንደሆነም የኮሚሽኑ የውጭ ግንኙነትን የሚመሩት ባለሥልጣን ገልጸዋል።

"ጊዜው አሁን በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የሦስትዮሽ ድርድር መፍትሔ እንዲገኝ ተግባራዊ ምላሽ መስጫ እንጂ፤ ውጥረቶችን መጨመሪያ አይደለም" ብለዋል። 

ኅብረቱ በወቅቱ የአፍሪካ ኅብረት ሊቀመንበር የደቡብ አፍሪካው ፕሬዝዳንት ሲሪል ራማፎሳ አማካኝነት ተደራዳሪዎች ወደ መፍትሔ ለማምጣት እየተደረገ ላለው ጥረት ሙሉ ድጋፍ እንደሚሰጥም አስታውቀዋል።

በግድቡ ዙሪያ የሚካሄደው ድርድር በፍጥነት መጀመር እንዳለበትና ውይይቱ ስኬታማ በሆነ መልኩ ይጠናቃቃል ብሎ እንደሚጠበቅም ምክትል ፕሬዝዳንቱ አስታውቀዋል።

ኅብረቱ ከዚህ በፊት ባወጣቸው መግለጫዎች ኢትዮጵያ፣ ሱዳንና ግብፅ በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ዙሪያ ያላቸውን አለመግባባቶች በውይይት ፈተው መግባባት ላይ እንዲደርሱ ሲገልጽ ነበር።

በአፍሪካ ኅብረት አደራዳሪነት የሚካሄደው የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የሦስትዮሽ ድርድር መቋረጡ ይታወቃል።

ኢትዮጵያ በግድቡ ላይ የሚደረገው ድርድር በውጤት እንዲጠናቀቀቅ ፍላጎቷ መሆኑን ደጋግማ አስታውቃለች።

ድርድሩ የተቋረጠው በሌሎቹ ተደራዳሪ አገሮች ምክንያት እንደሆነም ስትገልጽ ነበር።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም