ኢትዮጵያዊያን ብሔራዊ ጥቅምና ሉዓላዊነት ላይ አንድ ሆነን በጋራ መቆም አለብን - ምክትል ከንቲባ አዳነች አቤቤ - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያዊያን ብሔራዊ ጥቅምና ሉዓላዊነት ላይ አንድ ሆነን በጋራ መቆም አለብን - ምክትል ከንቲባ አዳነች አቤቤ
አዲስ አበባ ጥቅምት 14/2013 (ኢዜአ) ኢትዮጵያዊያን የውስጥ ችግር ቢኖርም ብሔራዊ ጥቅምና ሉዓላዊነት ላይ በአንድነት መቆም አለብን ሲሉ የአዲስ አበባ ምክትል ከንቲባ አዳነች አቤቤ ተናገሩ።
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የሕዳሴ ግድብን አስመልክተው አወዛጋቢ አስተያየት ሰጥተዋል።
ፕሬዚዳንቱ በንግግራቸው "ግብፆች የሕዳሴውን ግድብ ያፈነዱታል" ማለታቸው በርካታ ኢትዮጵያዊያንና የኢትዮጵያን ወዳጆችን አስቆጥቷል።
የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ አዳነች አቤቤ ከኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ጋር በነበራቸው ቆይታ ኢትዮጵያዊያን ከመቼውም ጊዜ በላይ በአንድነት እንቁም ብለዋል።
ምክትል ከንቲባዋ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብን በተመለከተ የሰነዘሩት አስተያየት የግድቡ ባለቤቶች በሆኑት ኢትዮጵያዊያን ዘንድ ፈጽሞ ተቀባይነት እንደሌለው አጽኖኦት ሰጥተዋል።
ግድቡ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ከዕለት ጉርሱ ቀንሶ እየገነባው ያለና የሕልውናው ፕሮጀክት በመሆኑ የራሱን ሀብት ለመጠቀም የማንንም ፈቃድ አይፈልግም ብለዋል።
ኢትዮጵያዊያን በራሳችን ሀብት እንዳንጠቀም በውስጥ ችግሮች ተጠምደን እንድንበጣበጥ ከሚያደርጉ አካላት መንቃት ያለብን ጊዜው አሁን ነው ብለዋል ምክትል ከንቲባዋ።
የቱንም ያህል የውስጥ ችግሮች ቢኖሩ ኢትዮጵያዊ በብሔራዊ ጥቅምና ሉዓላዊነት ጉዳይ አይደራደርም፤ የቀደመው የአገር ፍቅርና መቆርቆር በዚህ ትውልድም አለ ሲሉ ገልጸዋል።
ኢትዮጵያዊያን አንድ ሆነን ከተነሳን የሚበግረን ኃይል የሌለ በመሆኑ በጋራ መቆም ይገባናል ብለዋል።