በግድቡ ዙሪያ የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም ለማስከበርና ውዥንብሮችን ለማጥራት አስፈላጊው ሁሉ ይደረጋል ... አምባሳደር ዲና ሙፍቲ - ኢዜአ አማርኛ
በግድቡ ዙሪያ የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም ለማስከበርና ውዥንብሮችን ለማጥራት አስፈላጊው ሁሉ ይደረጋል ... አምባሳደር ዲና ሙፍቲ
አዲስ አበባ ጥቅምት 14/2013 (ኢዜአ) በሕዳሴ ግድብ ዙሪያ የሚፈጠሩ ውዥንብሮችን ለማጥራትና የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም ለማስከበር አስፈላጊው ርቀት ይኬዳል ሲሉ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ተናገሩ።
የአሜሪካው ፕሬዚደንት ዶናልድ ትራምፕ በሕዳሴ ግድብ ውሀ ሙሌት ዙሪያ አወዛጋቢ ትችት ሰንዝረዋል።
ይህን ተከትሎም የጠቅላይ ሚኒስቴር ጽህፈት ቤት "በምንምና በማንም ካሰብነው መንገድ አንቀርም ያቀድነውን ከማሳካት የሚያግደን ምድራዊ ኃይል የለም" የሚል አቋም የያዘ መግለጫ አውጥቷል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ለኢዜአ እንደገለጹትም ፕሬዚዳንት ትራምፕ በሕዳሴ ግድቡ ዙሪያ የተናገሩት ተገቢነት የሌለውና ሊሆን የማይችል ነው።
መንግስት በዚህ ጉዳይ የማያወላውል ግልጽና ጠንካራ አቋም አለው ብለዋል አምባሳደር ዲና።
የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም በውጪውም ዓለም ለማስከበር በዋናነት በየአገራቱ የሚገኙ ኤምባሲዎችና ቆንስላ ጽህፈት ቤቶች እንዲሁም የተለያዩ አጋር ተቋማት እንቅስቃሴ እያደረጉ እንደሆነም ጠቁመዋል።
ከጎረቤት አገራት ጋር ያለውን ግንኙነት የማጠናከር ስራዎች እየተሰሩ መሆኑንም አክለዋል።
በመካከለኛው ምስራቅ፣ በአውሮጳ፣ በእስያና በሰሜንና በላቲን አሜሪካ ጭምር የኢትዮጵያን ጥቅም ሊያስከብር በሚችል ሁኔታ እንቅስቃሴዎች እየተደረጉ ነው ብለዋል።
በግድቡ ዙሪያ ጠንካራ የዲፕሎማሲ ስራዎችን በመስራት ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ስለ ግድቡ በሚገባ እንዲያውቅና ዓላማውንም እንዲረዳ ለማድረግ ብሎም የሚፈጠሩ ውዥንብሮችን ለማጥራት አሁንም ስራዎች ይሰራሉ ነው ያሉት።
ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ላይ የሰነዘሩትን አስተያየት ምሁራንና ባለሙያዎች እንዲሁም የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ጭምር እየተቹትም ነው።
የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ የፕሬዚዳንቱ ንግግር ሃላፊነት የጎደለውና መነሻ ግንዛቤ የሌለው እንደሆነ ነው የገለጹት።
"ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊያን በእንዲህ አይነት ሀላፊነት የጎደለው አነጋገር ፍርሀት አይገባቸውም፣ ታሪክ ሁሉንም ያስተምራል" ብለዋል።
የአሜሪካ ህግ አውጪ ምክር ቤት /ኮንግረስ/ አባል የሆኑት ዴሞክራቱ ጄሰን ክሮው የፕሬዚዳንት ትራምፕን ንግግር ከተቹት መካከል ይገኙበታል።
ጄሰን ክሮው በትዊተር ገፃቸው ባሰፈሩት መልዕክት የፕሬዚደንቱን ንግግር "በግዴለሽነትና ካለመረጃ የተደረገ ነው" ሲሉ ተናግረዋል።
አሜሪካ ሀቀኛ አደራዳሪ በመሆን የዲፕሎማቲክ ስምምነት ላይ እንዲደረስ ማድረግ አለባትም ብለዋል።
ስሜት አይሰጥም ሲሉ የገለጹትን የእርዳታ ማቋረጥ ሃሳብ መተው አለባቸውም ብለዋል ጄሰን ክሮው።