ፋና ጠንካራ ጎኑን በመደመርና ድክመቱን በመቀነስ በአንድነትና አብሮነት እሴቶች ላይ ሊሰራ ይገባዋል - አቶ ንጉሡ ጥላሁን - ኢዜአ አማርኛ
ፋና ጠንካራ ጎኑን በመደመርና ድክመቱን በመቀነስ በአንድነትና አብሮነት እሴቶች ላይ ሊሰራ ይገባዋል - አቶ ንጉሡ ጥላሁን
አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 14/2013(ኢዜአ) ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጠንካራ ጎኑን በመደመርና የነበረበትን ድክመት በመቀነስ በአንድነትና አብሮነት እሴቶች ላይ መስራት እንዳለበት የድርጅቱ የቦርድ ሰብሳቢ አቶ ንጉሱ ጥላሁን አሳሰቡ፡፡
ተቋሙ 25ኛ ዓመቱን ሲያከብር በሃሳብ ልዕልና ላይ ተመሰርቶ ተመራጭና ተደማጭነቱን አጠናክሮ ለመቀጠል ቃል የሚገባበት አጋጣሚ እንደሆነ ተገልጿል።
የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት የቦርድ ሰብሳቢ አቶ ንግሱ ጥላሁንን ጨምሮ የሚዲያ ተቋማት ኃላፊዎችና የዘርፉ ባለሙያዎች በታደሙበት የተመሰረተበትን 25ኛ ዓመት እያከበረ ነው።
በኢትዮጵያ የልማት፣ የሠላምና የዴሞክራሲ ጎዳና ጠንካራና ደካማ ጎኖች እንዳሉት ጠቅሰው፤ የኢትዮጵያ የሚዲያ ድክመትና ጥንካሬ 25 ዓመታትን ባስቆጠረው ፋና ውስጥ ይታያል ብለዋል።
የኢትዮጵያዊያን የአንድነትና አብሮነት ነባር እሴቶች ባለመጠበቃቸው ጥላቻና ቂም በቀል ለመዘራቱ መገናኛ ብዙሃን የራሳቸው ሚና እንደነበራቸው አንስተዋል።
በዚህም የነበሩ ስህተቶችን በማረም ለወደፊት ለመተለም ሚዲያዎች ራሳቸውን መመርመርና መፈተሽ የወቅቱ ጥያቄ ነው ብለዋል።
በአንድነትና አብሮነት የጋራ እሴቶች ላይ መስራት እንዳለባቸውም ተናግረዋል።
ፋና ለአገረ መንግስት ግንባታ ከፍተኛ ሚና የተጫወተ ሚዲያ እንደሆነ የገለፁት አቶ ንጉሡ፤ ከትንሽ ተነስቶ ትልቅ መሆንን ያሳየ፣ ተደራሽነቱን በማስፋት፣ ከአገር አልፎ ለተቀረው ዓለም የገጽታ ግንባታ ስራዎችን መጀመሩን አድንቀዋል።
በቀጣይም በተሰበረው የኢትዮጵያዊያን አንድነትና አብሮነት እሴቶች ላይ ድልድዩን መገንባት፣ የጥላቻ ግንብን በማፍረስ እንደስሙ ፋና ወጊ መሆን እንዳለበት ጠቁመዋል።
የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ጌታቸው ድንቁ ፋና ኢትዮጵያ ውስጥ በሕዝብ ተመራጭና ተደማጭ ከሆኑ ሚዲያዎች አንዱ መሆኑን ጠቅሰው መንግስት የሚዲያውን ዘርፍ የህግ ማዕቀፍ በማሻሻል የብሮድካስት ሚዲያውን መቆጣጠር ብቻ ሳይሆን ማልማት ላይ እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
በቀጣይም መረጃ በመስጠት፣ ለዴሞክራሲ ምቹ መደላድል በመፍጠር፣ ብሔራዊ መግባባትና አሳታፊ ግልጽ አስተዳደር እንዲኖር ብሎም የዜጎች ባህልና እሴት እንዲዳብር በማስተዋወቅ ሃላፊነቱን እንዲወጣ ጠይቀዋል።
የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ አድማሱ ዳምጠው በበኩላቸው ፋና አሳታፊና ሞጋች አዲስ አስተሳሰብ የፈጠረ፣ ሰርቶ መለወጥ እንደሚቻል ያሳየ፣ ሙያን ያስተማረ፣ ተወዳዳሪ፣ ተመራጭና ተደማጭ በመሆን ፈር ቀዳጅ የግል ሚዲያ መሆኑን ተናግረዋል።
25ኛ ዓመቱን ሲያከብር የሃሳብ ፍጭትና በትውልድ ቀረጻ ላይ ያተኮሩ የለውጥ ፍላጎቶችን በማስቀጠል ሃላፊነቱን ለመወጣት ቃል እንደሚገባም ገልጸዋል።
ፋና ብሮድካስቲን ኮርፖሬሽን የዛሬ 25 ዓመት ሕዳር 12 ቀን 1987 ዓ.ም በአማርኛና አሮምኛ ቋንቋዎች በሳምንት ለ38 ደቂቃዎች ነበር የሬዲዮ ስርጭቱን የጀመረው።
ዛሬ በ11 የክልል ኤፍ.ኤም ጣቢያዎችና በሰባት ቋንቋዎች በሳምንት ለአንድ ሺህ ሠዓታት ለአድማጭ ተመልካቾቹ ተደራሽ ስለመሆኑ ተነግሯል።