ቀጥታ፡

ፕሬዝዳንት ትራምፕ ግድቡን አስመልክተው በሰጡት መግለጫ ላይ ኢትዮጵያ ማብራሪያ ጠየቀች

አዲስ አበባ ጥቅምት 14/2013 (ኢዜአ) ኢትዮጵያ የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ትናንት ታላቁን የህዳሴ ግድብ በማስመልከት በሰጡት የተሳሳተ መግለጫ ዙሪያ ማብራሪያ ጠየቀች።

የኢፌዴሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ገዱ አንዳርጋቸው ዛሬ በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር ማይክ ሬይነር፤ፕሬዝዳንት ትራምፕ የህዳሴ ግድቡን አስመልክተው በሰጡት መግለጫ ላይ ኢትዮጵያ ማብራሪያ እንደምትፈልግ ጠርተው አነጋግረዋል።

ፕሬዝዳንት ትራምፕ ከሱዳን እና ከእስራኤል መንግስታት መሪዎች ጋር በስልክ ባደረጉት ውይይት ታላቁን የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ አስመልክተው የተናገሯቸው ንግግሮች ሀላፊነት የጎደላቸው ናቸው በሚል በርካቶች ተችተውታዋል።

ሚኒስትሩ አቶ ገዱ በዚህ ወቅት በግድቡ እና በድርድሩ ሂደት ዙሪያ የተሰጠው መግለጫ ትክክል ያልሆነ እና የተሳሳተ ነው፤የአባይን ውሃ ፍሰት አያቆምም ብለዋል፡፡

በኢትዮጵያ እና በግብፅ መካከል ጦርነት መቀስቀሱ ፤ በኢትዮጵያ እና በአሜሪካ መካከል ያለውን የረጅም ጊዜ አጋርነት እና ስትራቴጂካዊ ህብረት የሚያንፀባርቅ አይደለም።

እንዲሁም የፕሬዝዳንቱ ሀሳብ በአለም አቀፍ ህጎችም ተቀባይነት የለውም ነው ያሉት፡፡

አቶ ገዱ አንዳርጋቸው አያይዘውም ኢትዮጵያ በሉዓላዊነቷ ላይ ለሚሰነዘሩ አደጋዎች እንደማትንበረከክና እና ወደፊትም በግድቡ ላይ በአፍሪካ ህብረት ማዕቀፍ ስር ለሚደረጉ የሶስትዮሽ ድርድሮች ለመቀጠል ቁርጠኛ መሆኗን አስታውቀዋል፡፡

ምንጭ-የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም